“መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጎ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ሚኒስቴሩ በሳምንቱ 9ሺህ 902 ዜጎች ከሳውዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ችሏል ብለዋል።
ከተባበሩት መንግስታት የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ፣ የሰላም ግንባታ ጉዳዮች እና ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር ግርሃም ሜይትላንድ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር እንደመከሩም አምባሳደር ዲና አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሰላም ግንባታ ከተሳተፉ ሀገራት ከፍተኛ ሚና ያላት መሆኑም ተጠቅሷል።
ውይይቱ በአብዬ የሚገኘውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ስትራቴጂክ ግምገማና ተልዕኮውን መልሶ ማዋቀር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደነበር አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።
በተለይ ሱዳን በአብዬ የሚገኘው የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲወጣ መጠየቋን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በሱዳን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ አንዲወጣ ከተፈለገ ከአብይ ግዛት ደረጃውን እና መስፈርቱን አሟልቶ አንዲወጣ ምክክር እንደሚደረግም በውይይቱ ተነስቷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ከጆርዳን አምባሳደር ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን የአረብ ሊግ በህዳሴ ግድብ ላይ የያዘው አቋም የተሳሳተ መሆኑን እንደገለጹላቸው አምባሳደር ዲና አብራርተዋል፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነትም ከአክሱም ዘመን ጀመሮ የቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል።
ሌላው በመግለጫው የተጠቀሰው በሳምንቱ የምሥራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) መደበኛ ያልሆ ስብሰባ ማድረጉ ነው፡፡ በዚህም 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተሳካ እንደነበር አንዲሁም በጅቡቲ የምርጫው ሂደት መልካም መኾኑ ተገልጿል።
በዚህ ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ ማስከበር ሂደቱ የተናጥላዊ የተኩስ አቁም በመንግሥት ብቻ የተደረገ እንደሆነም ተነስቷል። በዚህም ለደቡብ ኤስያ ሀገራት አምባሳደሮች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል ነው የተባለው፡፡
በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ፣ አንዲሁም በሰሜን እና ላቲን አሜሪካ የሚገኙ ኢምባሲዎች 60 ሀገራት በበየነ መረብ ማብራሪታ ተደርጎላቸዋል።
መከላከያ ሠራዊት መውጣቱ መልካም ጅማሮዎች እና በጎ ምላሾች እየታዩ እንደሆኑ ቃል አቀባዩ አብራርተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ቻይና፣ አሜሪካ፣ ሩሲያና ሌሎችም ሀገራት በይፋ በሁኔታው ላይ በጎ ምላሽ ሰጥተዋ ብለዋል፡፡
አምባሳደር ዲና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተም ከሳውዲ አረቢያ ያሉ ዜጎችን ለማስመለስ ግብረ ኀይል ሄዶ የኢትዮጵያን ኢምባሲ እያገዘ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- አንዱአለም መናን-ከአዲስ አባባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post “መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ መንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጎ ምላሽ መስጠት ጀምረዋል” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.