
“የፌዴራል መንግሥት የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይዟል” የመተከል ዞን
ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 24/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከመተከል ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን
የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ከሰሞኑ መግለጹን አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ዜጎች መፈናቀላቸው ደግሞ ሰባዊ፣
ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን አስከትሎ አልፏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የዞኑ ኮማንድ ፖስትና የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ
የሥራ ኃላፊዎች ከተፈናቃዮች ጋር ባደረጉት ተደጋጋሚ ውይይት ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው መደበኛ ሕይወት እንዲኖሩ
እየተደረገ ነው፡፡
የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ አባል አቶ በትግሉ ተስፋዬ ለአሚኮ በስልክ እንደተናገሩት በቻግኒ ራንች ጊዚያዊ
መጠለያ የነበሩ ተፈናቃዮች ሙሉ በሙሉ ተመልሰዋል፡፡ ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ዜጎችም እስከ አሁን ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች
ምግብና ቁሳቁስ በማቅርብ ቀና ትብብር እንዳደረጉላቸው ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይም ረጂ ድርጅቶችና መንግሥት ለተፈናቃዮቹ ዕለታዊ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ለተፈናቃዮች የዕለት ምግቦችን
ከማድረስ ጎን ለጎን የአካባቢው ባሕልና ሥነ ሥራዓት በሚፈቅደው መሠረት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማሌዎችና
የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት የእርቀ ሰላም ሥነ-ስርዓት መደረጉን አቶ በትግሉ ተናግረዋል፡፡
እርቀ ሰላሙ በነዋሪዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠርና ፊታቸውን ወደ ልማት እንዲያዞሩ ያስችላል ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ ተረጋግተው እንዲኖሩ በጸጥታ ኀይሎች ጥበቃ እየተደረገላቸውና ምንም አይነት የፀጥታ ስጋት አለመኖሩን አቶ
በትግሉ አስረድተዋል፡፡
ለተፈናቃዮቹ የመጠለያ፣ የመጸዳጃ ቤት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃና የሕክምና አገልግሎት እንደተሟላላቸውም ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ወቅት በዳንጉር፣ በቡለን፣ በድባጤና በማንዱራ ወረዳዎች መኖር ጀምረዋል ነው ያሉት አቶ በትግሉ።
በተፈናቃዮች ማዕከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለእርሻ ልማት የሚውሉ ትራክተሮችን በማቅረብ ማልማት መጀመራቸውን
ተናግረዋል፡፡
በተለይም ከማንዱራ ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደ መደበኛ ሥራቸው ለመመለስ የሚያስችል ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ነው
የተናገሩት፡፡ በቀጣይ ዜጎች በዘላቂነት እስከሚቋቋሙ ድርስ የሁለቱ ክልሎች መንግሥታት የጋራ ግብረ ኀይል ድጋፉን አጠናክሮ
እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ሥራውን ለማሳለጥ ሲባል በመተከል ዞን የጋራ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ይቋቋማል ብለዋል፡፡ የሚቋቋመው ጽሕፈት ቤት ተፈናቃዮች
ወደ መደበኛ ሥራ እስከሚገቡ ድርስ ችግሮቻቸውን እየተከታተለ ይፈታል፣ ማስተካከያ ርምጃም ይወስዳል ነው ያሉት፡፡
“የፌዴራል መንግሥትም የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መድቧል”
ብለዋል፡፡ ይህም ተፈናቃዮቹ መደበኛ ሕይወት መኖር እንዲጀምሩ ይደግፋቸዋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
The post “የፌዴራል መንግሥት የመተከል ዞን ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ይዟል” የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ቴክኒክ ኮሚቴ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.