“ሁለት ተሰጡ ሁለቱንም ሰጡ”
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 23/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገር ፍቅሩ ሲገባ፣ ታሪክ በደም ሥር ሲጋባ፣ ለወገን መሰጠት ለእናት ሀገር ሁሉንም መስጠት። ለእናት ሀገር መሞት እድለኛነት፣ ስለ ሀገር መኖር ኩራት፣ ሀገር መጠበቅ ጀግንነት ነው ይላል ወታደር። ኑሮው በዋሻ አዳሩ በዱር፣ መነሻው ሀገር መድረሻውም ሀገር፣ ሕልሙ ክብር፣ ስኬቱም ነፃ ሀገር፣ የደመቀ የታሪክ ምስክር ነው። ሳይነኩት የማይነካ፣ ሲከጅሉት የማያስነካ፣ ጀግንነቱ የማይለካ ነው የኢትዮጵያ ወታደር።
ኢትዮጵያ በውስጡ አለች፣ ኢትዮጵያዊነት፣ አይበገሬነት፣ ታጋሽነት፣ አሸናፊነት የወታደሩ መለያዎች ናቸው። ስለ መለዮ ክብር፣ ስለ ሠንደቅ ፍቅር ሲል፣ ደም ያፈስሳል፣ አጥንት ይከሰክሳል፣ አምሳለ ቀስተ ደመና፣ የተስፋ ምልክት፣ የአሸናፊነት አርማ፣ የነፃነት ሕብር ዜማ፣ የምሕረት ቃል ኪዳን፣ የመከራ ዘመን መሻገሪያ የማይናወፅ መርከብ ስለሆነው ሠንደቅ ሕይወቱን ይሰጣል። ጀግንነት የአባት ውርስ፣ አሸናፊነት ረቂቅ ቅርስ፣ ነፃነት አብሪ የክብር ልብስ፣ ድል ድግስ ነው ለዚያ ጀግና።
ጠላቶች ምስጢሩ ቢጠፋባቸው፣ ኃያልነቱ ቢሰወርባቸው፣ አሰፈሪነቱ ባይገለጥላቸው ነክተው ያስነሱታል፣ ሲነሳ ፈርተው ይተውታል። አንተስ ጀግና ነህ ብለው እጅ ይነሱለታል።

“ካባቱ ባድማ የተኛውን በሬ፣
እየቀሰቀሱ አደረጉት አውሬ” እንደተባለው ሲነኩት አውሬ ይሆናል፤ የማይሸነፍ የማይረታ። ልጆቿ በአንድነት ወደ ፈጣሪ ምልጃ ያቀርቡላታል፣ ፈጣሪ በምሕረት ዓይኑ ይመለከታታል፣ በኃይሉ ይጠብቃታል፣ ለዓለም ምስክር፣ ክብር፣ የውቅያኖስ መክፈያ በተር ትሆን ዘንድ ጠብቆ ያኖራታል። ዝቅ እናድርጋት የሚሉትን አዋርዶ ከፍ ያደርጋታል፣ በዙሪያ ገባው ማዕበል አደረግንባት፣ ከእንግዲህ መሻገሪያ የላትም ወዮላት ለሚሉት በግሩም ጥበብ፣ በአስፈሪ ኃይል ያሻግራታል።
ኢትዮጵያዊ ድንበር አልፎ አይወርም፤ ከድንበር ወዲህ አያሻግርም። ሞቱ ከድንበር መቃብሩም ከሠንደቁ ሥር ይሆናል እንጂ ሀገሩን ለሚደፍር ቦታ አይሰጥም። ኢትዮጵያውያን ከሚሰባሰቡበት፣ ጥላቻና መከፋፈል ከሚቀበርበት፣ ኢትዮጵያን ማስከበርና ከፍ ማድረግ ከሚመከርበት፣ ጀግና ጀግና ከሚመረጥበት፣ መከታ እንደ ቡቃያ ከሚኮተኮትበት፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ አሸናፊነት፣ ስለ ኀያልነት ከሚሰበክበት፣ ተኩስና መታገስ፣ ኢትዮጵያዊነትና ፅናት ከሚቀሰምበት ከተዋበ ምድር ተገኝቻለሁ።
በዚያ አስደናቂ ምድር ኢትዮጵያ ተደጋግማ ትጠራለች፣ ሀገር ትወደሳለች፣ ከምንም በላይ ትከብራለች። እድል ቀንቶኝ በዚያ ሥፍራ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እየዘመሩ፣ ኢትዮጵያን ሊያስከብሩ፣ ኢትዮጵያውያንን ሊያኮሩ የተዘጋጁ ወታደሮች ሲመረቁ አየሁ። በፅናታቸው፣ በኅብረታቸው፣ በወኔያቸው፣ በሀገር ፍቅራቸው ተደምሜያለሁ። እነርሱን ዓይቼ ራሴን ተመለከትኩት፣ ኢትዮጵያ የሠጠችኝ ብዙ ነገር አለ፣ እኔ ግን ምንም አልሰጠኋትም። ምንም አልሰጠሁሽምና ይቅር በይኝ እናቴ፣ ለአንቺ ምንም ቢሰጡሽ የሚያንስብሽ እንጂ የማይበዛብሽ፣ ከፍ ብለሽ የኖርሽ፣ ከፍ ብለሽ የምትኖሪ፣ በሰውና በፈጣሪ መንፈሳዊ ቅርርብ የምትከበሪ ነሽና ለአንቺ ሁሉንም የሰጠሽ የታደለ ነው አልኩ።
እነርሱ ግን ለወለደቻቸው እናት፣ እትብታቸው ላረፈችባት ምድር፣ ታሪኳ ከፍ ብሎ ለተቀመጠ ሀገር ዋጋ ሊከፍሉ፣ ምን ሰጠሽኝ ሳይሆን ምን እንስጥሽ እያሉ ተዘጋጅተዋል። በሥርዓት ተሠድረው ሲመለከቷቸው ሀገሬ ሆይ ምን እንስጥሽ ፍቅር፣ ክብር ወይስ ሕይወት የሚሉ ይመስላሉ። በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ብዙ የገረሙኝ ነገሮችን ተመለከትኩ። ከሁሉም በላይ ቀልቤ በአንደኛው አረፈ። ለሀገራቸውና ለወገናቸው ሕይወት ለመስጠት ቃል ኪዳን ካሰሩት መካከል የአንድ እናት ልጆች ቃል ኪዳን ሳበኝ።
ምንም እንኳ በዚያ ሥፍራ የተሰባሰቡት፣ በኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሠፈሩት ሁሉም የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች ቢሆኑም የእነዚህ ደግሞ ከአንዲት ኢትዮጵያዊት እናት ማኅፀን የተገኙ፣ ለአንዲት ሀገር በአንድ ማሰልጠኛ ተቋም የሠለጠኑ ነበሩና አስገረመኝ። በወታደር ምርቃት ወላጆች ተገኝተው የአበባ ጉንጉን ሲሰጡ፣ በጋራ ደስታቸውን ሲገልጡ አይታይም። በብርሸለቆ ግን ወታደሮቹ ሲመረቁ እናታቸው ለልጆቻቸው እንኳን ለዚህ በቃችሁ፣ እንኳን ደስ አላችሁ፣ እንኳንም አደረሳችሁ ሲሉ የአበባ ጉንጉን ሰጧቸው።
ጀግና ሆነው እንዲኖሩ አበረታቷቸው፤ መልካሙን ሁሉ ተመኙላቸው።
ይህ ትዕይንት እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን አስገርሟል። ልጆቹ እንባ ከዓይናቸው እየፈሰሰ፣ የወላጅ እናትና የውድ ሀገር ፍቅር በአንጀታቸው እየተላወሰ አደራውን ተቀበሉ።
ሻለቃ ፅጌ አርዓያ ይባላሉ። ወታደር ናቸው። በውትድርና ዓለም ኢትዮጵያን ከ20 ዓመታት በላይ አገልግለዋል፣ አሁንም እያገለገሉ ነው። በብዙ ግንባሮች ተሰልፈዋል። ሀገርና ሕዝብ የሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት ሲፈፅሙ ኖረዋል። ፈጣሪ ሕይወታቸው እንዲሞላ፣ ዘመናቸው እንዲሰላ፣ ከአብራካቸው ሁለት ፍሬዎችን ሰጣቸው። እርሳቸውም አመስግነው ተቀበሉ፣ አጀግነው አሳደጉ። በውትድርና ሕይወታቸው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ልጆቻቸውንም አብረው ይወስዷቸው ነበር። ጀግና ወታደር፣ መልካም እናት፣ የፅናት፣ የአሸናፊነት፣ ሀገር በሴት ትመሰላለች እንዲሉ የሀገር ተምሳሌት ናቸውና ልጆቻቸው እናታቸውን ይከተሉ ጀመር። በደስታ አደጉ። እናታቸው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ የዘወትር ምኞታቸው ቢሆንም ወታደር ይሆናሉ የሚል ግምት አልነበራቸውም። ልጆቹ ግን በውስጣቸው ያለው ወታደርና ሀገር የሚለው ነበር።
ሻለቃ ፅጌ ስለ ልጆቻቸው ሲናገሩ “ከእኔ ጋር ስላደጉ ሙሉ በሙሉ ወታደር ይሆናሉ የሚል ግምት አልነበረኝም፣ ነገር ግን ቢገቡ ደግሞ አልጠላውም፣ ማንኛውም እናት ይሄ ቢሆንልኝ ብላ እንደምትመኘው እኔም ሌላ እመኝላቸው ነበረ፣ ልጆቹ ግን እናታችን መከላከያ ሆነን ሀገራችን ነው ማገልገል ነው የምንፈልገው ሲሉ ደስተኛ ሆንኩኝ። የእነርሱም የእኔም ፍላጎት ስላለበት፣ በቃ ይሁን ብዬ ደስተኛ ሆኜ ሸኘኋቸው” ነበር ያሉኝ።

ሻለቃ ፅጌ ሁለት ልጆች ተሰጥቷቸው፣ ሁለቱንም ለሀገራቸው ስጦታ ሰጡ፣ የእናትነት ናፍቆት፣ የልጅ ስስት ቢኖርም ከእናት ሀገር የሚበልጥ ነገር የለምና ሁሉንም ቻሉት። ነገሩ የእናትነትን አንጀት የሚፈታተን ነው ለእርሳቸው ግን ተችሏል። እናቶች ልጆቻቸው ወደ ሀገር መከላከያ ሲሄዱ ማዘኑ፣ መከፋቱ ማልቀሱም አይጠፋም።
ሻለቃ ፅጌ በዚህ ጉዳይ ላይ ሲናገሩ “ውትድርና መግባቴ ደስ ቢለኝም ሁለቱንም ወደ መከላከያ ስሸኛቸው፣ እንደ እናት የእናትነት ስሜት ነበረኝ፣ መከፋቴ ከእኔ ተለይተው መሄዳቸው፣ ከቤት መውጣታቸው ነው። ለትንሽ ቀን ከፍቶኝ ነበር፣ ከዚያ በኋላ ግን እኔም እንደዚያው ሆኜ ስለወጣሁ ተውኩት። እኔም እስካሁን በመካላከያ ሕይወት ጥሩ ደረጃ ነው ያለሁት፣ ምንም የጎደለብኝ ነገር የለም፣ እነርሱም የእኔን አርዓያ ተከትለው በመምጣታቸውና እኔ ከደረስኩበት በላይ እንደሚደርሱም ስለማምን ደስተኛ ሆንኩኝ” ነው ያሉት።
የልጅ ናፍቆት ቢጠናባቸውም፣ የልጆቻቸው የሀገር ፍቅር ስሜትና ወገን ወዳድነት ናፍቆታቸውን አስታገሰላቸው። “ልጆቼ መቼ እንደሚመረቁ ሳጣራ ነበር፣ መመረቂያቸውን ቀን ሳውቀው አስፈቅጄ መጣሁ፣ አሁን ልጆቼ ማስተር እንደተመረቁ ነው የምቆጥረው፣ ይህችን ቀን ደስታቸውን ልካፈል ስለፈለኩ መጣሁ” ያሉት ሻለቃ ደስታ ነበሩ።
ልጆቻቸው በያዙት ሙያ ከእሳቸው በላይ ሆነው ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ እና እንዲጠብቁ አደራ ሰጥተዋቸዋል። ሀገር ማለት እናት ማለት ናት፣ እናት ማለት ሀገር ስለሆነ ለእኔ ለእናታቸው ከሚሰጡት እንክብካቤ በላይ ለሀገራቸው እንዲሰጡም አደራ ሰጥቻቸዋለሁ ብለውኛል። “ልጆቼን ወደ ውትድርና ስሸኝ፣ አንዳንድ ሰዎች እንዴት ልጆችሽን ወደ ውትድርና ትሸኛቸዋለሽ፣ ለምን ላክሻቸው” ያሏቸው ሰዎች እንደነበሩም ነግረውኛል። “ውትድርና ማለት የማይገኝ ሙያ ነው፣ ምንም የማጎድልበት ነው፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ከውትድርና አሸሽተው ከመኖር እንደኔ መርቀው ቢልኳቸው ልጆቻቸው ጥሩ ደረጃ ይደርሳሉ” ነው ያሉት ሻለቃ ፅጌ። “የእኔን አርዓያ በመከተላቸው በጣም ነው ደስ ያለኝ፣ ዛሬ የተወለድኩበት ቀን ነው፣ በቅንነት እንደሚያገለግሉም እተማመንባቸዋለሁ” ሻለቃ ጽጌ ደስታቸውን ሲገልጹ።
ተመራቂዋ መሠረታዊ ወታደር ፋሲካ ኀይሌ “ከእናቴ ጋር ነው ያደኩት፣ በመከላከያ እጅ ውስጥ ነው ያደኩት፣ እናቴ የትም ቦታ ለሥራ ስትንቀሳቀስ አብሬ ኖሬያለሁ። የእርሷን ራእይ ተከትዬ እዚህ ደርሻለሁ፣ እናቴ ሀገሯን ስታገለግል ስለ ኖረች እኔም የእናቴን ራእይ ተከትዬ ሀገሬን ለማገልገል ቆርጬ ተነስቼ እዚህ ተገኝቻለሁ” ነው ያለችው። ፋሲካ ከወላጅ እናቷና ከውድ ሀገሯ አደራውን ተቀብለዋለች። በእናት መንገድ ለመሄድ ተዘጋጅታለች።
“እኔ ወታደር ለመሆን አስብ ነበር ፣ በምኞቴ መሠረት እዚህ ደርሻለሁ” ብላኛለች። ግሩም አስተዳደግ፣ ልጅንም ራስንም ለሀገር መስጠት።
የወታደር አንድነት፣ ፍቅር፣ ቅንነት ሲስባት እንዳደገም ነው የነገረችኝ። ኢትዮጵያ እና ውድ እናቷ የሰጧትን አደራ ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኗንም እንዲሁ።

“እናታችን ለእኛ የምትመኘው ምኞት ነበራት፣ እኛ ወታደር መሆንን ስንፈልግ ግን አላንገራገረችም፣ ችግር የለውም አለችን፣ እንዲያውም ጓደኞቻችን ሲሉን የነበረውን ፍርሃት እንድንቀርፍና ጠንካራ እንድንሆን አድርጋናለች” ሲልም ስለ እናቱ ነግሮኛል። “የሁለት እናት አደራ ነው የተቀበልኩ፣ በጣም ደስ ብሎኛል” ነው ያለኝ መሠረታዊ ወታደር ናትናኤል።
የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቅቆ፣ እናታቸው ልጆቻቸውን አቅፈው እየሳሙ ሸኟቸው። ልጆቻቸው ለሌላ ግዳጅ እሳቸውም ለሌላ ግዳጅ። ስሜቱ ይገርማል። ሲለያዩ በዝምታ ተመለከትኳቸው፣ የሚያስደነግጥ፣ የሚያሳዝን፣ በሌላ በኩል የሚገርም፣ የሚያኮራ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ይሰማኝ ነበር።
ብቻ ግን ልቤ አክብራቸዋለች። ነብሴ አድንቃቸዋለች። በአግራሞት እያየኋቸው ከአጠገቤ ራቁ። አይ ኢትዮጵያ መታደልሽ፣ የሚሳሳልሽ፣ የሚወድሽ፣ የሚያከብርሽ፣ የሚጠብቅሽ፣ ደጋግሞ ስምሽን የሚጠራሽ ሕዝብ ባለቤት ነሽ። እንደ ፈተናው መብዛት፣ እንደ ጠላት ክፋት፣ እንደ ክፉ ሥራ መበርከት የፀና ልጅ፣ የማይፈራ፣ በሀገር ጉዳይ የማያወላዳ ባይፈጠርልሽ ኖሮ አደጋው ከባድ ነበር። እኔ እኮራለሁ፣ እመካለሁ፣ እደሰታለሁ፣ በድንቅ ሀገር፣ ምስጢሯ በማይመረመር ውብ ሀገር ተወልጃለሁና።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post “ሁለት ተሰጡ ሁለቱንም ሰጡ” | አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.