
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 99ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
ባሕር ዳር፡ ሰኔ 23/ 2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 99ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ።
ምክር ቤቱ በቅድሚያ ከተወያየናቸው አጀንዳዎች መካከል ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር በተደረጉ በአራት የብድር ስምምነቶች ላይ አንዱ ነው፡፡ የመጀመሪያው የብድር ስምምነት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ያለውን ተደራሽነት የማሻሻል እና ለገጠሩ ኅብረተሰብ በቤተሰብ ደረጃ፣ ለማኅበራዊ ተቋማት እንዲሁም ለኢንተርፕራይዞች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለማሳደግ የሚውል ነው፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውለው ብድር 500 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡
ሁለተኛው የብድር ስምምነት ዓላማ የመሠረታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ማሻሻልና የተጠያቂነት ሥርዓትን ማጠናከር ሲሆን፣ በወረዳ ደረጃ የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና፣ የውኃ እና የገጠር መንገድ አቅርቦት መሠረታዊ አገልግሎቶች ተደራሽ ለማድረግና የሀገሪቱን ያልተማከለ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ለማጠናከር የሚያግዝ ነው፡፡ የብድር መጠኑም 250 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡
ሦስተኛው የብድር ስምምነት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ አማካኝነት የሚተገበር አነስተኛ እና መካከለኛ እንተርፕራይዞችን በፋይናንስ ለማጠናከር ለመደገፍ የሚውል ሲሆን የብድር መጠኑም 180 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡
አራተኛው የብድር ስምምነት የመረጃ ልውውጥ ቴክኖሎጂ በማዘመን ኢኮኖሚውን እና አጠቃላይ የመንግሥት አሠራርን ከተለመደው ባህላዊ የአሠራር ዘዴ ወደ ዲጂታል የመቀየር ሥራዎችን ለማስፈጸም የሚውል ሲሆን የብድር መጠኑን 200 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ነው፡፡ በድምሩ የ1 ቢሊየን 130 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር የብድር ስምምነቶች በማጽደቅ ረቂቅ አዋጆች ተደግፈው ቀርበዋል፡፡
ሁሉም ብድሮች ምንም አይነት ወለድ የማይታሰብባቸው፤ ባንኩ ብድሮቹን በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0.75% የአገልግሎት ክፍያ የሚታሰብባቸው ሆነው የ6 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱም ከሀገሪቱ የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣሙ እና ምንም አይነት ተጓዳኝ ጫና የሌላቸው መሆኑን በማረጋገጥ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ረቂቅ አዋጆቹ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የአፍሪካ የመንገድ ደኅንነት ቻርተር እና የተባበሩት መንግሥታት የመንገድ ትራፊክ ኮንቬንሽን ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቷል፡፡
የነዚህ ሁለት ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መጽደቅ ሀገሪቱ በመንገድ ትራንስፖርት ረገድ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት የሚያሳልጥ ከመሆኑም በላይ ብሔራዊ፣ አካባቢያዊና አህጉራዊ የመንገድ ደኅንነት ፕሮግራሞችን በቅንጅት ለመፈጸም የሚያስችል እንዲሁም በሀገር ደረጃ ሰፊና ሁሉን አቀፍ የሆኑ የመንገድ ደኅንነት ፖሊሲዎች እንዲቀረጹ የሚያስችል መሆኑ ታምኖበት ለምክር ቤቱ ይሁንታ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በጥልቀት ከተወያያ በኋላ በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
The post የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 99ኛ መደበኛ ስብሰባ በሁለት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ። first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.