
በብሔርና በሃይማኖት ካባ ሕዝብን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚቀሰቅሱ አካላትን በጋራ መታገል እንደሚገባ የከሚሴ ከተማ
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ።
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 22/2013 ዓ.ም (አብመድ) የከተማዋ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እንደተናገሩት ከሰሞኑ
በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የብሔርም ሆነ የሃይማኖት
መሠረት የለውም።
ይሁን እንጂ የጸጥታ ችግሩ ሃይማኖት እና ብሔር ሳይለይ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነልቦናዊ ቀውስ የፈጠረ መሆኑን
ተናግረዋል።
የሕዝብን የአብሮነት ዕሴት በመሸርሸር ድርና ማግ ሆኖ እልፍ ዘመናትን የኖረ ሕዝብን በፓለቲካ ሴራ በብሔርና በሃይማኖት
ለመከፋፈል የሚደረግ ማንኛውንም እንቅስቃሴ በጋራ መከላከል እንደሚገባም
የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች አስገንዝበዋል።
የከሚሴ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አደም መሀመዴ እንደተናገሩት ከጥንት ጀምሮ የቆየው የሕዝቡ አንድነት አሁንም ተጠናክሮ
ቀጥሏል። ሰላም፣ አንድነት፣ ወንድማማችነት፣ መተሳሰብና መከባበር በሕዝብ ዘንድ መኖሩን አንስተዋል። ከሰሞኑ በተከሰተው
የጸጥታ ችግር በአማራና በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰዋል። በነበረው የጸጥታ ችግርም ሕዝብን ለመከፋፈል
መሠራቱንም ተናግረዋል። በመሆኑም ሕዝቡ የሴረኞች መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባዋል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልዓከ ገነት ደጀን
ተስፋዬ የብሔረሰብ አስተዳደሩ ነዋሪዎች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁለንተናዊ መስተጋብራቸው በአንድነት፣ በፍቅር እና
በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች የሰላም መደፍረስ ችግር እንደሚስተዋል
ገልጸዋል።
የጸጥታ ችግሩ የብሔርና የሃይማኖት ቅርጽ እንዲይዝ መደረጉ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።
የመሪዎች አለመግባባትና አለመደማመጥ በመንፈሳዊ አስተምህሮ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን የተናገሩት መልዓከ ገነት ደጀን
እየተኮተኮተ ያደገው የብሔር ፖለቲካ ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ፣ ሀገሪቷንም ወደማትወጣው አዘቅት ሳይወስድ መፍትሔ
ሊፈለግ እንደሚገባ መክረዋል። ችግር ሲውልና ሲያድር እየጠነከረ እንደሚሄድ የገለጹት መልዓከ ገነት ደጀን ለዘመናት የኖረ
የሕዝብ አንድነትን ለማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትን መሥራት እንዳለበት መክረዋል።
የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ተወካይ ፓስተር ተሾመ ደምሴ “የከሚሴ ሕዝብ በችግርም ውስጥ ሆኖ አንዱ
ለሌላው ያስባል”ብለዋል፤ የጸጥታ ችግሩ ከማኅበረሰቡ ውጪ የተፈጠረ መሆኑንም ነው የተናገሩት። መንግሥት ውስጣዊ
አሠራሩን በደንብ መፈተሽ እና ከሕዝብ ጋር ጥብቅ ትስስር መፍጠር እንደሚጠበቅበትም መክረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎችም የሕዝቡን አንድነትና የመከባበር ዕሴት ማዳበር ይጠበቅባቸዋል፤ ፖለቲከኞችም
ከከፋፋይ አጀንዳ ሊወጡ እንደሚገባም ፓስተር ተሾመ ጠይቀዋል።
የከሚሴ ወንጌላዊት መካነየሱስ መሪ ቄስ ቦካ አብደታ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በጋራ መሥራት እንደሚገባና በሰለጠነ መልኩ
የመፍታት ልምድ መፈጠር አለበት ብለዋል።
የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎቹ ትውልዱ የሃይማኖት አባቶችን አስተምህሮ ሊያከብርና ሊተገብር እንደሚገባም
መክረዋል። ከጽንፈኛ ፖለቲከኞችና ከከፋፋይ የመገናኛ ብዙኃን ተጽዕኖ ራስን ነጻ ማድረግም ይገባል ነው ያሉት።
ከሰሞኑ በከሚሴ ከተማ የጸጥታ ችግር መፈጠሩ ይታወሳል፤ ከተማዋ አሁን ወደ ቀድሞ ሰላሟ ተመልሳለች። መደበኛ ማኅበራዊና
ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም ተጀምሯል። የመንግሥት ተቋማት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የንግድ ተቋማትና ሌሎች ዘርፎችም
ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው ተመልሰዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ — ከከሚሴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
The post በብሔርና በሃይማኖት ካባ ሕዝብን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚቀሰቅሱ አካላትን በጋራ መታገል እንደሚገባ የከሚሴ ከተማ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች አሳሰቡ። first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.