“የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኅበረሰብ እንገንባ!”
ባሕር ዳር: የካቲት 27/2013 ዓ.ም (አብመድ) በየዓመቱ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት መጋቢት 8 እና በኢትዮጵያዊያን የዘመን ቀመር ደግሞ የካቲት 29 “የዓለም ሴቶች ቀን” ይከበራል፤ ቀኑ በተደጋጋሚ “ማርች 8” እየተባለ ሲጠራም እንሰማለን፡፡
የዘንድሮው የዓለም የሴቶች ቀን “የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኅበረሰብ እንገንባ!” በሚል መሪ መልዕክት በዓለም ለ110ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡ በአማራ ክልልም የካቲት 30/2013 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ከክልሉ ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአማራ ክልል የሚከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሁለት ዐበይት ክንውኖች አሉት ያሉት የሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ወይዘሮ ምጥን ብርሃኑ ናቸው፡፡ ዝግጅቱ የሴቶችን የሀገር ግንባታ አበርክቶ እውቅና መስጠት የመጀመሪያው ነው፡፡ ለቀሪዎቹ መነሳሳትን የሚፈጥር እና አበርክቷቸውን የታሪክ አንዱ አካል በማድረግ በጽሑፍ እንዲሰፍር ማድረግ ደግሞ ሁለተኛው፡፡
ወይዘሮ ምጥን እንዳሉት በመርኃ ግብሩ ላይ የሀገሪቱ ርእሰ ብሔር፣ ሚኒስትሮች፣ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ በክልሉ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራንና የሥራ ኀላፊዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሴት አደረጃጀቶች እና የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዕለቱም ሴቶች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ የሚዳስስ ውይይት ይካሄዳል፤ አበርክቷቸውን የሚመጥን የታሪክ ሰነድ ዝግጅት ላይም የጋራ መግባባት ላይ ይደረሳል ብለዋል የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ፡፡
“የጀግኒት ሽልማት” በሚል በተለያየ ደረጃ አርዓያ የሆኑ፣ የተሻለ አበርክቶ የነበራቸው እና ሞዴል የሆኑ ሴቶች ተሸላሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
ስምንተኛ ክፍልን በተሻለ ውጤት ያለፉ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተሻለ ውጤት የተመረቁ ተማሪዎች፣ ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች፣ ሥራ ፈጣሪ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች፣ በክልሉ ውስጥ ባሉ ዞኖች ሞዴል ሴት መሪዎች፣ ተቋሙን በተለያየ ጊዜ በመሪነት ያገለገሉ እና ጉልህ አስተዋፅኦ ያላቸው አጋር አካላት እውቅና ይሰጣቸዋል ነው ያሉት ወይዘሮ ምጥን፡፡
በሀገሪቱ የሴቶች ጭቆና ስር የሰደደ እና ለዘመናት የተንሰራፋ እንደነበር ወይዘሮ ምጥን ጠቅሰዋል፡፡ በአንድ ጀምበር አስተሳሰቡን ሰብሮ መሻገር ከባድ ቢሆንም ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ግን መካድ እንደማይቻልም ነው ያስረዱት፡፡
በዓሉ ሲከበርም በሴቶች ተሳትፎ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት እና የአመራር ሰጭነት ሚና ላይ ለውጥ እየፈጠሩ ለመሄድ በሚያግዝ መልኩ የሚዘጋጅ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post “የሴቶችን መብት የሚያከብር ማኅበረሰብ እንገንባ!” first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.