አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፋሰስ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ እየተሰጠ ነው።
ለሁለት ቀናት በሚሰጠው ስልጠና ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው።
ስልጠናው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ተፈጥሮ ሃብት መጠበቅ፣ መጠቀምና ማስተዳደር ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እንደሚረዳ የተፋስስ ልማት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ግዛው ተናግረዋል ።
በስልጠናው ከአዲስ አባባ እና መቐለ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የተውጣጡ ምሁራን ጥናት የሚያቀርቡ ይሆናል፡፡
የስልጠና መርሃ ግብሩን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ነው ያዘጋጀው፡፡
በመድረኩ ዶክር ጌቴ ዘለቀ የመሬት መራቆት መንስኤና የሚያስከትለውን ጉዳት በተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አስተዳደር ሥርዐት ጠንካራ አለመሆን፣ የተከለሉ የደን ቦታዎች መመንጠርና የሰወች ሰፈራ፣ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖር፣ የኢንዱስትሪ ግንባታ የተደራጀ ማስተር ፕላን አለመኖር፣ ያልተመጠነ የህዝብ ብዛት፣ የአስተራረስ ዘይቤ አለመቀየር፣ ስለ መሬት መራቆት ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የተቋማት አደረጃጀት መቀያየርና አለመቀናጀት፣ የመረጃ ልውውጥ ክፍተት ጉድለት እና የሚሠሩ ሥራዎች ዘላቂ አለመሆን ለመሬት መራቆት መንስኤ መሆናቸውን ነው የጠቀሱት፡፡
የተራቆተ መሬት ዝናብ ሲዘንብ በጎርፍ ምክንያት እንደሚናድ፣ የሚታረስ መሬት እንደሚጎዳ፣ መንደሮችንና መሠረተ ልማትን እንደሚያወድም፣ ግድቦች በደል ስለሚሞሉ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚሆኑ እና ሃይቆችን እስከማድረቅ የሚደርስ ጉዳት እንደሚያስከትልም ጠቅሰዋል፡፡
በቀጣይም የመገናኛ ብዙሃን የሚመለከታቸውን አካላት ማነቃቃትና ማሣወቅ፣ የመንግስት አካላትን መሞገት እንዲሁም ጥናታዊ ግኝቶችን ትርጉም ባለውና በቀላል የተግባቦት ዘዴ ማቅረብ ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡
የመሬት መራቆት ለኢትዮጵያ ተጨባጭ አደጋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም መጋፈጥ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሚተከሉ ችግኞች መጽደቅ እንዳለባቸውና ለዚህም ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
የመገናኛ ብዙሃንም ይህን እውነታ ተረድተው 27 በመቶ ያህል ከድህነት ወለል በታች የሚኖረውን ህዝብ ህይወት መቀየር እንዲቻል በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መረጃ ማቅረብና ተፈፃሚነቱን በመከተል መዘገብ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
በተመስገን ገ/ህይወት
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡
The post በተፋሰስ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በቢሾፍቱ እየተሰጠ ነው first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.