
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሃት በሃገሪቱ ላይ የደህንነት ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል ሙሉ ለሙሉ መደምሰሱን የመከላከያ የሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጄነራል ባጫ ደበሌ ገለጹ፡፡
ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ ከክፍሉ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ ጁንታው ከሰሜን ዕዝ የዘረፋቸውን የሃገር መጠበቂያ ትጥቆች ይዞ ለመዋጋት ቢሞክርም ሰራዊቱ በጀግንነትና አይበገሬነት በሶስት ሳምንት ውስጥ የመደበኛ ውጊያ መዋጋት እንዳይችል አድርጎ ደምስሶታል ብለዋል፡፡
በመደበኛ ውጊያ ተመቶ የተበታተነው የጁንታው ሃይል በሽምቅ ውጊያ ለመዋጋት ቢሞክርም ሰራዊቱ የጁንታውን አውራ አመራሮችና ተዋጊዎቹን ከተደበቁበት ዋሻና ጎሬ እየለቃቀሙ በመደምሰስ እና ለህግ በማቅረብ የፈፀመው ግዳጅ የተሳካ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት የጁንታው ቡድን በመደበኛም ይሁን በሽምቅ የመዋጋት አቅም እንዳይኖረው አድርጎ በመደምሰሱ የጥፋት ሃይሉ አማራጭ ያደረገው የውሸት ፕሮፖጋንዳ በመስራት ህዝቡ ውስጥ ገብቶ ህፃናትንና አዛውንትን ከፊት አስቀድሞ መዋጋትን መምረጡን አውስተዋል፡፡
ሰራዊቱ በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር 8 ወር ሲቆይ ህዝቡ የሰላም ተጠቃሚ እንዲሆንና ሰብአዊ አገልግሎቶችና ድጋፎች ለህዝብ እንዲደርሱ መስዋዕትነትን በመክፈል ጭምር ያገለገለ ቢሆንም ከህዝቡ የተሰጠው ምላሽ ግን በተቃራኒው ሆኗል ነው ያሉት፡፡
የህዝቡን ፍላጎት ለማሟላትና የጥሞና ጊዜ ለመስጠት መንግስት በወሰነው ውሳኔ መሰረት ሰራዊቱ መቐለን ለቆ ሲወጣ በህዝብ መሃል ተደብቆ የነበረው የጁንታው ሃይል መሃል ከተማ ወጥቶ ጨፈረ እንጂ ከሰራዊቱ ጋር አልተዋጋም የመወጋትም አቅምም የለውም ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
The post አሸባሪው ህወሃት ለኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት ሆኖ እንዳይቀጥል ሙሉ ለሙሉ ተደምስሷል-ሌ/ጄ ባጫ ደበሌ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.