በአማራ ክልል በጅምር የቀሩ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ውኃ፣መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 29/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተጀመሩ የንጹህ መጠጥ የውኃ ተቋማት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ለውኃ ወለድ በሽታ መጋለጣቸውን አሚኮ ያነጋገራቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል፡፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ታች አርማጭሆ ወረዳ የፍል ውኃ ከተማ ነዋሪው ዳዊት ምናለ እንደነገረን የከተማዋ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታ በ2006 ዓ.ም ተጀምሮ ዛሬም አልተጠናቀቀም፡፡
ለ2 ሺህ 600 ሰዎች አገልግሎት የሚሰጥ 50 ሺህ ሊትር ውኃ የመያዝ አቅም ያለው ታንከርም በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቷል፡፡ በወቅቱ የተዘረጋው የውኃ ማስተላለፊያ ከአካባቢው የአየር ንብረት ጋር እንደማይሄድ ነዋሪዎች ቢያመለክቱም ተግባራዊ ስላልተደረገ በሙቀት ምክንያት ለብልሽት መዳረጉን ተናግረዋል፡፡
በ2009 ዓ.ም ለክልሉ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ጥያቄውን አቅርበው እንደሚፈታላቸው ቢነገራቸውም እስከ አሁን መፍትሄ አለማግኘታቸውን ነው አቶ ዳዊት የተናገሩት፡፡
በተመሳሳይ በጠለምት ወረዳም የደጃች ሜዳ ነዋሪዎችን የቤት ለቤት የንጹህ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ ለማድረግ በ2009 ዓ.ም ሥራ ተጀምሮ ነበር። 75 በመቶ የውኃ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ፣ 10 በመቶ የቦኖ ሥራ እና የውኃ ማጠራቀሚያ ታንከር ግንባታ ተጠናቅቋል፡፡ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት እንደነበር የወቅቱ የጠለምት ወረዳ ውኃ ሀብት ልማት እና ኢነርጅ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብርሃም ታጀበ በ2012 መጨረሻ ለአሚኮ ተናግረው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ውኃውን ለመግፋት የሚያገለግለው ጀነሬተር ዋጋ አቅራቢው በጨረታ ካሸነፈበት ዋጋ ጋር ባለመመጣጠኑ ተግባራዊ አለመደረጉን ነበር አቶ አብርሃም በወቅቱ የተናገሩት።
የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አደም ወርቁ በወቅቱ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ፕሮጀክቱ በ2013 በጀት ዓመት ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ምላሽ ሰጥተው ነበር። ይሁን እንጅ እስከ አሁን ድረስ ችግሩ አለመፈታቱን ነዋሪዎቹ ነግረውናል፡፡
እነዚህን ወረዳዎች እንደ አብነት አነሳን እንጅ በታች አርማጭሆ ፈንድቃ፣ በላይ ጋይንት ጋንጋ ጨጨሆ፣ አይና ቡግና፣ በምዕራብ ጎንደር ባሻየና መሻህና በመሳሰሉ የክልሉ አካባቢዎች ተጀምረው የቆሙ የውኃ ተቋማት ዛሬም መፍትሔ አልተሰጣቸውም፡፡
በዚህም ምክንያት እናቶች፣ አረጋውያን እና ህጻናት እስከ አራት ኪሎ ሜትር በመጓዝ የወንዝ ውኃ ለመጠቀም ተገድደዋል፡፡ ለውኃ ወለድ በሽታ መጋለጣቸውንም ነግረውናል፡፡ ችግሩ እንዲፈታ ከወረዳ ውኃ ሀብት ልማት እና ኢነርጅ ጽሕፈት ቤት እስከ ክልል ውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ልማት ቢሮ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበው መፍትሄ አለማግኘታቸውን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ዳይሬክተር ኤፍሬም ምኒሽር ስለጉዳዩ ተጠይቀው በክልሉ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተጀመሩ በርካታ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ዛሬም እንዳልተጠናቀቁ አረጋግጠዋል፡፡ የጥናትና ዲዛይን፣ የቴክኖሎጂ መረጣ፣ የተቋራጭ አቅም ውስንነት፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ የውል አስተዳደር ውስንነት ለችግሩ በምክንያትነት ተቀምጠዋል፡፡ የፕሮጀክቶች ጥናት ሲካሄድ እና ከተገነቡም በኋላ የነበረው የውኃ አቅም በተፈጥሮ ሃብት መመናመን ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነስም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዓለም ባንክ ፕሮግራም ተይዘው ከነበሩት ከ100 በላይ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከ 60 በመቶ በላይ የሚሆኑት በዲዛይን ችግር ውላቸው እንዲቋረጥ መደረጉንም አንስተዋል፡፡ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ 32 ተቋማት ከ 500 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል ብለዋል፡፡
በመጀመሪያው የዋሽ ፕሮግራም በ 560 ሚሊዮን ብር በፌዴራል መንግሥት ወጭ ለመገንባት ተይዘው የነበሩ ሰላሳ ሁለት የውኃ ተቋማት በወቅቱ ባለመጠናቀቃቸው ገንዘቡን የክልሉ መንግሥት እንዲሸፍን ተጠይቋል፡፡ በዚህ ወቅትም በዲዛይን ችግር ምክንያት ከተቋረጡት ተቋማት ውስጥ ከተወሰኑት በስተቀር በመገንባት ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የታች አርማጭሆን የንጹህ መጠጥ ውኃ ችግር በተመለከተ ግን እውቅና እንደሌላቸው ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡ ምዕራብ ጎንደር ዞን እንደ ባሻየና መሻህ፤ በሰሜን ጎንደር ዞን ደጃች ሜዳ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋማት ውላቸው ተቋርጧል፤ በበጀት ችግርም ለተቋራጭ ውል አለመሰጠቱንም ነግረውናል፡፡
የአይና ቡግና የውኃ ችግር ደግሞ በዲዛይን ችግር የተፈጠረ ሳይሆን በውኃ መጠን መቀነስ የተከሰተ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ችግሩን ለመፍታት በአካባቢው በቅርብ ርቀት ተደጋጋሚ ጥናት ተደርጎ ውኃ ማግኘት አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡ ችግሩን በጊዜያዊነት ለመፍታት ከ‹ኦስትሪያ ዲቨለፕመንት ኤጀንሲ› በተገኘ ድጋፍ የማሻሻያ ሥራ ለማከናወን ውል ተይዟል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ግን ግድብ መሥራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
በላይጋይንት የጋንጋ እና የጨጨሆ የውኃ ፕሮጀክት ችግሮችን ለመፍታት ወረዳው በላከው ጥናት መሰረት ለጥገና የሚውል 600 ሺህ ብር ተመድቦ የጥገና ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በወራት ውስጥም ተጠናቅቆ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የሚታየውን የጥናትና የዲዛይን ችግር ለመፍታት ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ በተጨማሪ የአማራ ዲዛይን እና የላሊበላ አማካሪ ድርጅቶች ፕሮጀክቶችን በመገምገም ለትግበራ የማዘጋጀት ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡ የተቋሙን ባለሙያዎች አቅም የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ ከፍተኛ የውኃ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ደግሞ ግድቦችን በመሥራት የማኅበረሰቡን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በቀጣይ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል፡፡
መንግሥትም ለተፈጥሮ ሃብት ሥራ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አንደሚገባው መክረዋል፡፡ እነዚህን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ውጤታማ ማድርግ ካልተቻለ ግን የውኃ ችግሩ ከዚህም በላይ የከፋ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል የንጹህ መጠጥ ውኃ ሽፋን 66 ነጥብ 2 በመቶ መድረሱን ከክልሉ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post በአማራ ክልል በጅምር የቀሩ የንጹህ መጠጥ ውኃ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ውኃ፣መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.