
በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን በላይ ትኩረት ያላገኙ የኅብረተስብ ክፍሎች የሥራ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር መፈጠር
እንዳለበት የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 28/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ከአጋር አካላት ጋር ባለፉት ስምንት ወራት የተከናዎኑ
ተግባራትን ገምግሟል፡፡ በግምገማው እንደተገለጸው ባለፉት ስምንት ወራት ሥራ ሊፈጠርላቸው ከሚገቡ 20 ሚሊየን ትኩረት
ያላገኙ የማኅረስብ ክፍሎች ውስጥ ሁለት በመቶ ብቻ የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተገልጿል፤ ቀሪዎቹ 98 በመቶ የሚሆኑት
አካል ጉዳቶች፣ ሴቶች ፣ ስደተኞች እና ተፈናቃዮች ልዩ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ተመላክቷል፡፡
የፌዴራል የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ንጉሡ ጥላሁን፣ ባለፉት ስድስት ወራት ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ እድል
መፈጠሩን ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥ 38 በመቶው ጊዜያዊ የሥራ እድል ሲሆን 62 በመቶው ደግሞ ቋሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም በሀገሪቱ አሁን ካለው የሥራ አጥ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ለሥራ ፈጠራ በቀጣይም ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል አቶ
ንጉሡ።
የሥራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ
በተለይ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት። የቋሚ የሥራ እድል ተጠቃሚነትን
80 በመቶ ለማድረስ እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ ቋሚ የሥራ እድል እውን ለማድረግ ከግልና ከመንግሥት ተቋማት፣ ከኢንዱስትሪዎችና ከፋብሪካዎች ጋር የቅንጅት ሥራ
በስፋት ይከናወናል ብለዋል። ከሌሎች ሀገራት ልምድ በመውሰድም አዳዲስ የሥራ መስኮችን ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች
ይደረጋሉ ነው ያሉት።
በኮሮናቫይረስ ሳቢያ በርካታ የሥራ እድሎች አለመፈጠራቸውን አስታውሰው፣ ችግሩን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ወደ
ሥራ ለመቀየር የሚያስችል ዝግጁነት እንደሚያስፈልግና የሚፈጠሩ ሥራዎችን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ማጣጣም የሚያስችል
አቅምን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኮሚሽኑ በሥራ እድል ፈጠራ ላይ በተለያዩ ተቋማት በኩል ተናቦ መሥራት ላይ የሚታይ ክፍተት መኖሩን አንስተው በተቀናጀ
መንገድ ትኩረት ያላገኙ የኅብረተስብ ክፍሎች የሥራ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር መፈጠር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
አቶ ንጉሡ በኢትዮጵያ የሥራ አጥነት ችግርን ለማቃለል ከተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ጋር
በጋራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ2 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ ሥራ ፈላጊ ዜጎች ወደ ገበያው የሚቀላቀሉ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 200
ሺህ የሚሆኑት ከተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ናቸው።
የዓለማአቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ትኩረት ያላገኙ የኅብረተስብ ክፍሎች ወደ ሥራ
ባለመግባታቸው ሀገሪቱ 27 ቢሊየን ብር እንደምታጣ አመላክቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ባለ አለምየ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
The post በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን በላይ ትኩረት ያላገኙ የኅብረተስብ ክፍሎች የሥራ እድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት አሠራር መፈጠር እንዳለበት የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽን ገለጸ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.