የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በጢስ ዓባይ ሳተላይት ከተማ ተደራጅተው ለቆዩ ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አስረከበ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) ከተማ አሥተዳደሩ ዛሬ ከ40 በላይ ለሚሆኑ የመኖሪያ መስሪያ ቦታ ለማግኘት ተደራጅተው ለቆዩ ማኀበራት ነው ቦታውን ያስረከበው፡፡ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ካገኙት መካከል ሀብታሙ የሱፍ አንዱ ናቸው፤ ተደራጅተው ከቆዩ ከአራት ዓመታት በላይ ማስቆጠራቸውን ነግረውናል። የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ በማጣታቸው በቤት ኪራይ በየጊዜው መጨመር ምክንያት ሲቸገሩና ሲንገላቱ መቆየታቸውንም አስረድታል። ዛሬ በተሰጣቸው ቦታ መደሰታቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ከመፈጠሩ በፊት አስፈላጊ የሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከወዲሁ እንዲገነቡም ጠይቀዋል።
ሌላዋ ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የተሰጣታቸው ደግሞ ወይዘሮ ፍትፍቴ በላይ ናቸው። ዛሬ የመስሪያ ቦታ አግኝተው ያገኙትን ደስታ ለቀሪ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለሚጠይቁ ዜጎች ሁሉ ተመኝተዋል። “ከእንግዲህ የማስበው ቤቴን ገንብቼ የተረጋጋ ሕይወት መኖር ነው” በማለትም የረዥም ጊዜ ህልማቸው እንደተሳካላቸው ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በጢስ ዓባይ ሳተላይት ከተማ ተደራጅተው ለቆዩ 48 ማኅበራት (1 ሺህ 50 አባ ወራና እማ ወራዎች) ነው በተወካዮቻቸው አማካኝነት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ያስረከበው።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን መምሪያ የመሬት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ታረቀኝ የኋላ፣ በጢስ ዓባይ ሳተላይት ከተማ የአርሶ አደሮች ጥያቄ ከተፈታ በኋላ ማኅበራቱ ቦታቸዉን ሊረከቡ ችለዋል ብለዋል። ቦታ የተሰጣቸው ማኅበራት አስፈላጊ የሆኑትን የመሠረተ ልማት ግንባታ ጥያቄዎች በተደራጀ መልኩ መጠየቅ ይችላሉ ብለዋል።
የሚገነባው መሠረተ ልማት 30 በመቶ ከማኅበራት 70 በመቶ ከመንግሥት መሆኑንም ምክትል ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል። ወደፊትም ቢሆን የማኅበሩ አባላት በተለይ አመራሩ መጠናከር ይኖርበታል ብለዋል።
ሌሎች በከተማ አሥተዳደሩ ለሚገኙ ሳተላይት ከተሞች ለተደራጁ ማኅበራም ተመሳሳይ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ታረቀኝ በወቅቱ መሠራት የነበረባቸው ጉዳዮች ባለመሠራታቸው በዚህ ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ጫና ሊፈጥሩ ችለዋል ብለዋል። ሆኖም ግን ይህንን በማጣጣም እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
“የአርሶ አደሩን ካሳ ለመክፈል ትልቅ ተግዳሮት አለው፤ ወደ ሥራ ስንሰማራ በየቦታው የመብት ጥያቄ ይነሳል፤ይህን ሁሉ ጫና ተቋቁመንም ቢሆን እየሠራን እንገኛለን፤ ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ቦታ ይሰጠኝ የሚል ጥያቄ እያነሳ ነው፤ አዲስ የወጣው መመሪያ ግን አርሶ አደሩ ካሳ ከተከፈለው ቦታ ማግኘት የለበትም ይላል በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ አርሶ አደሩን በማይጎዳበት መልኩ የማጣጣም ሥራ እየሠራ ነው” ብለዋል።
አርሶ አደሩን በማይጎዳበት ሁኔታ መሬትን ከሦሰተኛ ወገን ነፃ ለማድረግ የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ በቦታው ተገኝተው ውይይት እያደረጉ እንደሆነ አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል።
አሁን ሕጋዊ እውቅና ካገኙ ማኅበራት ውጪ በከተማ አሥተዳደሩ የማደራጀት ሥልጣን ሳይሰጣቸው በዓዲስ መልኩ የሚያደራጁ አካላት ሕገ ወጥ ስለሆኑ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አቶ ታረቀኝ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር በጢስ ዓባይ ሳተላይት ከተማ ተደራጅተው ለቆዩ ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አስረከበ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.