Quantcast
Channel: The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

ያልታረመው ሥህተት። |የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

$
0
0

ያልታረመው ሥህተት።

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 21/2013 ዓ.ም (አብመድ) አቶ አመሸ ታረቀኝ በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ዝጎራ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ አመሸ የሰባት ልጆች አባት ናቸው፡፡ ኑሯቸው የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው፡፡ አቶ አመሸ ታኅሣሥ 26/2013 ዓ.ም በደረሰባቸው የትራፊክ አደጋ በሁለቱም ጉልበታቸው ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡ አቶ አመሸን በፈለገ ህይወት አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ላይ ነበር ያገኘናቸው፡፡ ልጆቻቸውን የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት ቢያደርጉም በደረሰባቸው አደጋ ኑሯቸው ተናግቷል፡፡

“ልጆቼን ለማስተማርና ህይወቴን ለመቀየር የነበረኝ ምኞት ህልም ሆኖ ቀረ፤ በመስኖ ለማምረት የቋጠርኩት ዘር እንደተሰቀለ” ቀረ ነው ያሉት በትካዜ፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን ቀንሰው ቢያሽከረክሩ፣ ሌሎች አካላትም የድርሻቸውን ቢወጡ ሲሉ ተማጽነዋል፡፡

ሌላው የትራፊክ አደጋ የደረሰበት ወጣት መሠረት አዳሙ ተወልዶ ያደገው በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ ነው፡፡ ወጣት መሰረት ባለትዳር ነው፡፡ ከቤተሰቦቹ ጋር ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሞ ወረዳ በዴሳ ቀበሌ ይኖራል፡፡ መሰረት የካቲት 10/2013 ዓ.ም በደረሰ የትራፊክ አደጋ አንድ እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ እስካሁን ለህክምና ብቻ ከ20 ሺህ ብር በላይ ወጭ አድርጓል፡፡ ጉዳቱ በመከሰቱ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ቤት ለመሥራት ያቀደው እቅድ ተስተጓጉሏል፡፡ መሰረት አሽከርካሪዎች በጥንቃቄ ጉድለት በሰው ህይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑንና ድርጊቱ ርምት ሊወሰድበት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡

በአማራ ከልል ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዋና ክፍል ኀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጽጌ አሻግሬ እንዳሉት

•በክልሉ ባለፉት ስምንት ወራት 1 ሺህ 500 የትራፊክ አደጋዎች ደርሰዋል

•በአደጋው የ807 ሰዎች ህይወት አልፏል

•በ694 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡

•ከ31 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሀገር ንብረትም ወድሟል፡፡

ለትራፊክ አደጋዎቹ መከሰት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም የአሽከርካሪዎች የብቃት ማነስ እና በፍጥነት ማሽከርከር በዋናነት እንደሚጠቀሱ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ገልጿል፡፡

በአማራ ክልል

•106 ሺህ 354 ተሽከርካሪዎች ተመዝግበው በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡

•ከተመዘገቡ ተሸከርካሪዎች ውስጥ 30 ሺህ 153 ተሽከርካሪዎች በክልሉ ባሉ 13 የምርመራ ተቋማት ዓመታዊ የቴክኒክ ምርመራ ያደረጉና ተለጣፊ ምልክት የወሰዱ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የትራንስፖርት ዘርፍ ተወካይ ምክትል ኀላፊ አቶ አበባው ታደሰ የቴክኒክ ምርመራ አድርገው ቦሎ ያላስለጠፉ ተሸከርካሪዎች ያላስለጠፉበት ምክንያት ተጣርቶ ከቀጣዩ ዓመት ጋር በቅጣት የሚያስለጥፉበት አሠራር መኖሩን ነግረውናል፡፡

እንደ አቶ አበባው ማብራሪያ በክልሉ 142 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የብቃት ማረጋገጫ ወስደው አሽከርካሪዎችን እያሰለጠኑ ነው፡፡ ነገር ግን በተጠናቀቁት ስድስት ወራት ቢሮው ባደረገው ቁጥጥር ካሉ 142 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ከሁለቱ ውጭ ሁሉም ማሰልጠኛ ተቋማት ችግር ያለባቸውና ከተቀመጠው መመዘኛ መስፈርት የወረዱ በመሆናቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል፡፡

አቶ አበባው እንዳሉት

•43 ማሰልጠኛ ተቋማት የቃል ማስጠንቀቂያ

•49 ማሰልጠኛ ተቋማት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ

•27 ማሰልጠኛ ተቋማት የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ

•9 ማሰልጠኛ ተቋማት የሦስት ወራት እገዳ የተጣለባቸው

•12 ማሰልጠኛ ተቋማት ደግሞ ፈቃዳቸው ሙሉ በሙሉ ተሰርዟል፡፡

አቶ አበባው በክልሉ የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ አዳዲስ ተሸከርካሪዎች ወደ ክልሉ ሲገቡ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ተገጥሞላቸው እየገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቀጣይ በክልሉ በሚገኙ ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መቆጣጠሪያ መሳሪያ ለማስገጠም እንቅስቃሴዎች መኖራቸውንና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እየተከናወነ ነግረውናል፡፡

አቶ አበባው በተጠናቀቁት ስድስት ወራት የደረሱት የትራፊክ አደጋዎች ባለፈው ዓመት ከደረሰው የትራፊክ አደጋ አኩአያ ሲታይ እየጨመረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“የትራፊክ አደጋ ለሀገርም ሆነ ለክልላችን አስጊ በመሆኑ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ አቅደን የግንዛቤ ፈጠራ እና የቁጥጥር ሥራ እየሠራን ነው” ብለዋል፡፡ በተጨማሪ በክልሉ ካሉ 62 የሕዝብ ትራንስፖርት ማኅበራት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ የበጀት እጥረት፣ የሰው ኃይል አናሳ መሆን የሚፈለገውን ውጤት እንዳይመጣ ማድረጉን በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡

ተወካይ ምክትል ኀላፊው እንዳሉት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ለአንድ ተቋም ብቻ መተው የለበትም፤ አሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ አለማሽከርከር፣ ማኅበረሠቡ የመንገድ ትራፊክ ሕጎችን በማክበርና ትርፍ ሆኖ ባለመጫን ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post ያልታረመው ሥህተት። | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

Trending Articles