“የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ከቀረበባቸው ክስ እና ወቀሳ ይልቅ በሕዝባቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ያሳስባቸዋል፡፡” የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) 1987 ዓ.ም የፀደቀው እና አሁንም በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያን በዘጠኝ ክልሎች እና በአንድ ከተማ አስተዳደር ያዋቅራታል፡፡ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላም ድሬድዋ ከተማ አስተዳደርን በቻርተር ኢትዮጵያን ካዋቀሯት ዘጠኝ ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች መካከል አንዷ ከተማ አስተዳደር አድርጎ አካተታት ያሉን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት መምህሩ አቶ ምስጋናው ጋሻው ናቸው፡፡
ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታትም ኢትዮጵያ በዘጠኝ ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች መንግሥታዊ እና አስተዳደራዊ መዋቅር ተመስርታ ቆይታለች፡፡ በቅርቡ ደግሞ ከ50 በላይ ብሔረሰቦችን ካቀፈው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አንዱ የሆነው ሲዳማ 10ኛው ክልል ሆኖ ተቋቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች እና በርካታ ቋንቋዎች የሚስተናገዱባት ህብረ ብሔራዊት ሀገር ናት፡፡ ማንነትን እና ቋንቋን መሰረት አድርጎ የክልል አስተዳደራዊ መዋቅርን የዘረጋው ሕገ መንግሥት ከ80 በላይ ክልሎች ለመመስረት የማይቻልበት የሕግ አመክንዮ እንደሌለው የሕግ ምሁሩ አስረድተዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 50 ንዑስ አንቀፅ 4 የአንድ ብሔር መጠሪያ በተሰጣቸው ክልሎች ውስጥ የተለያየ ማንነት ላላቸው ሕዝቦች የአካባቢያዊ አስተዳደር ማቋቋምን ስልጣን ለክልሉ ሰጥቷል፡፡
ቢሆንም ከአማራ ክልል ውጭ ይህንን ተግባራዊ ያደረገ ክልል አልነበረም ነው ያሉት አቶ ምስጋናው፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ጉራጌ እና ሌሎች የሚኖሩበት የኦሮሚያ ክልል ለአንዱም ብሔር እንኳ መሰል እውቅና እንዳልሰጠ አንስተዋል፡፡ ትግሬ፣ ኢሮብ እና ኩናማ በዋናነት የሚኖሩበት ትግራይ ለማንም ብሔረሰብ አካባቢያዊ አስተዳደርን አልፈቀደም፡፡ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሽናሻ፣ በርታ፣ አኝዋክ፣ ጉሙዝ እና መሰል ብሔረሰቦች የሚኖሩበት ቤንሻንጉል ጉሙዝ በሕገ መንግሥቱ የተወሰኑ ብሔረሰቦችን ስም ጠርቶ የፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ውክልና እና መሬትን ጨምሮ ባለቤትነት የእነዚህ ብሔሮች ብቻ ነው ሲል እንደሚደነግግ የሕግ መምህሩ አብራርተዋል፡፡ ይህ እውነት ዛሬም ያልተለወጠ እና መሬት ላይ ያለ ሃቅ እንደሆነ አቶ ምስጋናው ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሕዝቦች በክልላዊ ሕገ መንግሥታቸው ከሰጡት እውቅና በላይ ለዘመናት ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድም እህቶቻቸው ጋር አብረው እና ተዋደው ሀገር የመሰረቱ ሕዝቦች ስለመሆናቸው ድርሳናት በቂ ምስክሮች መሆናቸውን ያወሳሉ፡፡ በአንዳንድ እንደራሴዎች ከሰሞኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተደመጡ ክስ እና ውንጀላዎችንም “የሚያስተዛዝቡ ሃሳቦች” ብለዋቸዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት፣ ሕዝቦች እና የአማራ ልዩ ኀይል የተወነጀሉበት ሃሳብ ሀቁ መሬት የለም እንጂ ቢኖር እንኳን ከአንድ የሀገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት ከሆነ የሕዝብ እንደራሴ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር እና ሃይማኖትን ከሃይማኖት በሚያነሳሳ እና ኀላፊነት በጎደለው መልኩ መቅረብ አልነበረበትም ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱም የምክር ቤቱን የአሠራር እና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ መሰረት አድርጎ ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል በሥነ ስርዓት ሕጉ መሰረት ማስቆም ሲገባው ማስቀጠሉ ከንግግሩ በኋላ ላለው ውጤት ከተጠያቂነት አያድነውም ባይ ናቸው፡፡ ጉዳዩ በምክር ቤቱ አባላት እና በሕግ ሊታይ የሚገባውም እንደሆነ በመጥቀስ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምንም እንኳን በአንድ አካባቢ በሚኖር ሕዝብ ተመርጠው እና ተወክለው ወደ ምክር ቤቱ ቢገቡም የኢትዮጵያዊያን እንጂ የአንድ የተለየ ብሔር ተወካዮች አይደሉም ያሉት የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ አቶ መርሐፅድቅ መኮንን ናቸው፡፡ ከሰሞኑ በነበረው የምክር ቤት ስብሰባ ግን የተስተዋለው ከላይ ያነሳነውን የውክልና መርህ የተከተለ እንዳልነበረም አንስተዋል፡፡ የምክር ቤት እንደራሴዎች የሀገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን ባለቤት ሆነው ሳለ ስሜት የናጠው፣ ከሃቅ ያፈነገጠ እና የአንድን ሕዝብ ማንነት ያጠለሸ ሃሳብ በነፃነት እና ያለማንም ከልካይ ሲስተናገድ መስተዋሉን ተናግረዋል፡፡
ምክር ቤቱ የራሱ የሆነ የአሠራር ደንብ እና መመሪያ እንዳለው አቶ መርሐፅድቅ ጠቅሰዋል፡፡ በተወሰኑ እንደራሴዎች የቀረበው ሃሳብ ከእለቱ የምክር ቤቱ አጀንዳ ጋር የሚሄድ ባይሆንም እንኳን ከወቅታዊው የፀጥታ ችግር ጋር ሃሳቡን እንደሃሳብ መነሳቱን ከሕግ ሳይሆን ከቅንነት መቀበሉ እንደማይከፋም አንስተዋል፡፡ ነገር ግን ይላሉ አቶ መርሐፅድቅ መሰል ኀላፊነት የጎደለው ውንጀላ ሲቀርብ፣ ለግጭት የሚያነሳሳ ሃይማኖታዊ ትንኮሳ ሲንፀባረቅ እና ውለታው ያልተከፈለው የአማራ ልዩ ኀይል ሲብጠለጠል የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አለማስቆማቸው ትዝብት ላይ የሚጥል እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ጉዳዩ በቀጣይ በአግባቡ ታይቶ አስተዳደራዊ፣ ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች እንደሚያስፈልጉት ገልጸዋል፡፡
“የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ከቀረበባቸው ክስ እና ወቀሳ ይልቅ በሕዝባቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ያሳስባቸዋል” ነው ያሉት የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ፡፡ በስዓታት ልዩነት የእንደራሴዎቹ ውንጀላ እና የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ መግለጫ ተከታትለው መስተናገዳቸው ጉዳዩን ሰፋ አድርገን እንድንመለከተው ያስገድዳል ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ እና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ውህደት በፌዴራል መንግሥቱ እና በክልሎቹ መካከል በሰከነ መንገድ ሊመረመር የሚገባው እንደሆነም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post “የአማራ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ ከቀረበባቸው ክስ እና ወቀሳ ይልቅ በሕዝባቸው ላይ የደረሰው ጉዳት ያሳስባቸዋል፡፡” የርዕሰ መስተዳድሩ የሕግ ጉዳዮች አማካሪ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.