Quantcast
Channel: The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

ከሰሞኑ በሰሜን ሽዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰበት የቦርከና ወንዝ ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት አንዲሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

$
0
0

ከሰሞኑ በሰሜን ሽዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰበት የቦርከና ወንዝ ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት አንዲሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 20/2013 ዓ.ም (አብመድ) የቦርከና ወንዝ የብረት ድልድይ አንጾኪያ ገምዛ፣ ግሼ፣ አልብኮ እና ደዋ ጨፋ ወረዳዎችን ያገናኛል። ወደ ኬሚሴ፣ ደብረብርሃን፣ አዲስ አበባ እንዲሁም ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ወልዲያ መስመርም ወሳኝ መተላለፊያ ነው። ድልድዩ ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ነው።

በአካባቢው የሚመረትን የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ወደ ማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብም ብቸኛ አማራጭ ነው። የከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ መስተጋብር መሠረት የሆነው የቦርከና ወንዝ ድልድይ ቀደም ብሎ ከዕድሜ ብዛት የተነሳ ብልሽት አጋጥሞት ከባድ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ሳይችል የቆየ ቢሆንም ከሰሞኑ በተፈጠው የጸጥታ ችግር ደግሞ የድልድዩ ንጣፍ ተነቅሎ በመውደቁ ሙሉ በሙሉ ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል።

ድልድዩ ቀደም ብሎ ዕድሳት እንዲደረግለት ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር በአንጾኪያ ገምዛ እና በደዋ ጨፋ ወረዳዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለአብመድ ተናግረዋል። የኅብረተሰቡ ጥያቄ መሰረት ተደርጎ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳልተስተካከለ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የደዋ ጨፋ ወረዳ ተረፍ ቀበሌ አስተዳዳሪ ኢብራሂም አሊ ጠቁመዋል። በዚህም የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንደተገደበም ነው ያብራሩት።

የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የሀገር ሽማግሌና የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስተባባሪ አበራ ንጋቱ እንዳሉት ሰሞኑን የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ድልድዩ በደረሰበት ሰው ሠራሽ ችግር ከአገልግሎት ውጪ ሆኗል። የአብመድ የጋዜጠኞች ቡድንም በቦታው ተገኝቶ እውነታውን አረጋግጧል። በዚህም በጥቃቱ የተጎዱትን የኅብረተሰብ ክፍሎችም ሆነ ነብሰጡር እናቶችን በአቅራቢያ ወደሚገኝ የሕክምና ተቋም ለመላክ አስቸጋሪ ሆኗል።

በአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ሀገረማርያም ዋጨራ ቀበሌ የሚገኘው የመስኖ ጤና ጣቢያ ከወረዳው ነዋሪዎች በተጨማሪ በአዋሳኝ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር እና የኤፍራታና ግድም ወረዳ ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተለይ ሰሞኑን ደግሞ ከጸጥታ ችግሩ ጋር ተያይዞ የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ከፍተኛ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውንም ወደ ደሴ እና ኬሚሴ ሆስፒታሎች ይልካል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ የቦርከና ወንዝ የብረት ድልድይ መሰበሩን ተከትሎ ከፍተኛ የሕክምና ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሕሙማንን ወደተሻለ ሕክምና ለመላክ እንዳልተቻለ በጤና ጣቢያው የህክምና ባለሙያ ደጀን አዲሴ አስታውቀዋል። በቅርብ ርቀት የሕክምና አገልግሎት ማግኘት ሲቻል በመሀል ሜዳ በኩል ከ 160 ኪሎሜትር በላይ መዞር ግድ ሆኗል።

በዚህም በተለይ ከሰሞኑ በተፈጸመ ጥቃት የተጎዱ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የደም መፍሰስ አጋጥሟቸዋል፣ ወላዶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም መረዳት ተችሏል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚመለከተው የመንግሥት አካል አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ አስተያየት ሰጪዎች ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ ያጋጠመውን ብልሽት በተቻለ ፍጥነት ለማስተካከል እንቅስቃሴ እንደጀመረ አስታውቋል። በባለስልጣኑ የኮምቦልቻ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሳምሶን ተስፋዬ እንዳሉት የተበላሸውን የብረት ድልድይ ባለሙያዎች አይተውታል። የድልድዩ ተነጣፊ ብረት ሊቀየር እንደሚገባ የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል። መቀየር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ አስተዳዳሪ ጋር ውይይት መደረጉንም ጠቅሰዋል። በዲስትሪክቱ የተወሰነ ብረት መኖሩን የገለጹት ኢንጂነር ሳምሶን ተጨማሪ ብረት ከአዲስ አበባ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል።

ነገር ግን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት መዘግየቱን አመላክተዋል። ሙሉ በሙሉ አገልግሎቱ መቋረጡን ተከትሎ ግን ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም በፍጥነት እንደሚስተካከል ገልጸዋል። በተቻለ መጠን ከሁለት ሳምንት በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባም ነው የዲስትሪክቱ ሥራ አስኪያጅ የገለጹት። ለጊዜውም ቢሆንም ግን የአካባቢው ማኀበረሰብ እና አስተዳደሩ ጊዜ አዊ መተላለፊያ በመስራት ችግሩን ለመፍታ ጥረት ሲያደርጉ አብመድ ተመልክቷል፡፡

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ -ከመኮይ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post ከሰሞኑ በሰሜን ሽዋ ዞንና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰበት የቦርከና ወንዝ ድልድይ ተጠግኖ አገልግሎት አንዲሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎች ጠየቁ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

Trending Articles