
ጥቃቱ ቆሞ ሰላም እንዲፈጠር የጸጥታ አስከባሪ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ በአጣዬ ከተማ ከጥፋቱ የተረፉ ተጎጂዎች
ጠየቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአጣዬ የጥቃት ታሪክ በ2010 ዓ.ም ይጀምራል። በየጊዜው የሚነሱ ጥቃቶች
አጣዬን ጎድተዋታል፡፡ የመጀመሪያው ሀዘን አለቀ ሲባል ሌላ ሀዘን ይመጣባታል፡፡ አሁን የጥፋት ጊዜ አቆሟል ሲባል ሌላ ጥፋት
ይተካባታል፡፡ ሐዘኗ እየበዛባት፣ ደስታ እየራቀባት ተከታታይ ጊዜ ለማሰለፍ ተገደደች፡፡ አጣዬ ከአሁን በፊት ያሳለፈቻቸው ጥቃቶች
ሳይሽሩ፣ የወደሙ ተቋማት በደንብ ሳያንሰራሩ፣ በግፍ ወገኖቻቸውን ያጡ ዜጎች ሐዘናቸውን ሳይረሱ ሌላ ሐዘን ተሰጣት፡፡
መጋቢት 10/2013 ዓ.ም ምሽት 3 ሰዓት አካባቢ ሳይታሰብ በተከፈተው ጥቃት ጥፋት ደርሷል። ሰው ሞቷል፤ አካል ጎድሏል፤
ንበረት ወድሟል፤ ከቀዬ መፈናቀል፣ በስጋት መኖር መጥቷል፡፡ የጥቃቱ አጀማመርንና ጉዳቱን በተመለከተም አብመድ ተጎጂዎችን፣
ከተማ አስተዳደሩንና የኤፍራታና ግድም ወረዳ አስተዳደርን ጠይቋል።
“ጥቃቱ ከመድረሱ ከቀናት በፊት በስፍራው የነበረው የአማራ ልዩ ኀይል ለሌላ ግዳጅ ከቦታው እንዲነሳ ተደረገ” ይላሉ ነዋሪዎቹ።
የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ደምሰው መሸሻ በበኩላቸው ልዩ ኀይሉ ለሌላ ህግ ማስከበር ከወጣበት ቀን ጀምሮ
ጥቃቱ እንደጀመረ ተናግረዋል።
ልዩ ኀይሉ እንደተነሳም በአካባቢው ተደጋጋሚ የተኩስ ድምፅ ሲሰማ ከሰነበተ በኋላ መጋቢት 10 አመሻሽ ላይ በአጣዬ ከተማ
ከየት እንደመጡ የማይታወቁ ሰዎች በተሽከርካሪ ሆነው እየጨፈሩ ወደ አጣዬ ከተማ መግባት ጀመሩ፤ ማን ናችሁ? ተብለው
ሲጠየቁም ሰርገኞች ነን የሚል ምላሽ እንደሰጡ የወረዳው አስተዳዳሪ ተናግረዋል። ሰርገኞች ነን ባዮች ወደ ከተማዋ ከገቡ
በኋላም ጥይት መተኮስ ጀመሩ፤ እየመሸ ሲሄድ በስመ ሰርገኛ ወደ ከተማዋ የገቡት ጥፋት ደጋሾቹ የመጀመሪያውን ጥቃት በከባድ
መሳሪያቸው ታግዘው መፈፀም ጀመሩ። ሌሊቱን ሙሉም ከተማዋን በባሩድ ሲያጥኗት አደሩ ነው ያሉት።
ከጥቃቱ የተረፉ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ደግሞ ያች ምሽት የከፋ ሰቆቃ የተፈፀመባት ነበረች። አርብ ምሽት የጀመረው
ጥቃት ቅዳሜ ቀጥሎ ከተማዋ መውደም ጀመረች ነው የሚሉት የከተማዋ ነዋሪዎች ከአብመድ ጋር ባደረጉት ቆይታ። በዕለቱም
ንፁሃን ተገደሉ ንብረትም ወደመ፤ ሆቴሎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ድርጅቶች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ
ሱቆች፣ ተቃጥለዋል፣ ተዘርፈዋል፣ ከምንም በላይ ግን የማይተካ የሰው ህይወት ጠፍቷል ነው ያሉት።
አብመድ በስፍራው ተገኝቶ እንደታዘበውም በከተማዋ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። ከኔትወርክ መቋረጥን ጨምሮ በሌሎች
መሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት መድረሱን ተመልክቷል። ነዋሪዎችም ጥቃቱን የፈፀመው ቡድን ኦነግ ሸኔ የሚባል ታጣቂ ቡድን
እንደሆነ ገልጸውልናል። የከተማዋ ከንቲባ ደምስ አበበም የዚህ ጥቃት ቀያሽና ጥፋት አድራሹ ኦነግ ሸኔ እንደሆነ ግልፅ ነው
ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም አጣዬ ከገባችበት የሀዘን ድባብ አልወጣችም። እንቅስቃሴም ብዙ አይደለም። የፌዴራል ፖሊስና መከላከያ
ኀይል በአካባቢው ተሰማርቷል፤ በከተማዋ የጥይት ተኩስ ቆሟል። ይሁን እንጂ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በዙሪያ
ወረዳው አሁንም ጥቃቱ አልቆመም። በአላላና በረሀ ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች አሁንም ችግሩ አለ።
አብመድ ከወረዳውና ከከተማ አስተዳደሩ ከጥቃቱ ለማምለጥ የሸሹ በርካታ ወገኖችንም ተመልክቷል። እነዚህን ወገኖች መልሶ
የማቋቋም ሥራ እየተሠራም ነው ብለዋል ከንቲባው። ተጎጅዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚሠራው ሥራ ላይ የሁሉም ሚና
የሚያስፈልግ ቢሆንም የእለት ደራሽ ምግብና መሰል እርዳታ ማድረስ ስለሚያስፈልግ መንግሥት አስቸኳይ እርዳታ ሊያደርስ
እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከምንም በፊት ግን ጥቃቱ ቆሞ ሰላም እንዲፈጠር የጸጥታ አስከባሪ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ከጥቃቱ የተረፉ
ተጎጂዎች ጠይቀዋል።
ዘጋቢ:- ኤሊያስ ፈጠነ – ከአጣዬ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
The post ጥቃቱ ቆሞ ሰላም እንዲፈጠር የጸጥታ አስከባሪ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ በአጣዬ ከተማ ከጥፋቱ የተረፉ ተጎጂዎች ጠየቁ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.