Quantcast
Channel: The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

ለሀገር በከፈሉት ዋጋ ልክ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች መርጃ ማኀበር አባላት ተናገሩ፡፡

$
0
0


ለሀገር በከፈሉት ዋጋ ልክ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች መርጃ ማኀበር አባላት ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) መቶ አለቃ ኃይሉ አዲሱ ተወልደው ያደጉት በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር
ጋዝጊብላ ወረዳ ነው፡፡ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ በተካሄዱ ጦርነቶች ተሳትፈዋል፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም ተሳትፈው አንድ
እጃቸው እና እግራቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በወቅቱ በነበረው ሂደት መንግሥት መቋቋሚያ ሰባት ሺህ ብር ቢሰጣቸውም
በነበረባቸው የአካል መጉደል ችግር ተጨማሪ ሥራ ሠርተው ራሳቸውን መለወጥ ባለመቻላቸው ጎዳና ላይ ለመኖር ተገደው ነበር፡፡
ነገር ግን የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች መርጃ ማኀበር ተቋቁሞ ባደረገላቸው ድጋፍ እንዲሁም የሚኖሩበት አካባቢ ማህበረሰብ
ባደረገላቸው ድጋፍ ጎዳና ላይ ተነስተው ኑሯቸውን እየመሩ ነው፡፡ መቶ አለቃ ኃይሉ ማኀበሩ በየዓመቱ የሚሰጣቸውን 9 ሺህ 600
ብር ተጠቅመው ሁለት ልጆቻቸውን እያስተማሩ ቢሆንም ለሀገር በከፈሉት መስዋዕትነት ልክ ሀገራቸው እየከፈለቻቸው እንዳልሆነ
ይናገራሉ፡፡
መንግሥት ለጦር ጉዳተኞች ለሀገር በከፈሉት መስዋዕትነት ልክ እያገዘን አይደለም የሚሉት መቶ አለቃ ኃይሉ የሀገርን ዳር ድንበር
ለሚያሥጠብቁ በተደረገላቸው አሸኛኘት ልክ ሲመለሱም ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ዘርፌ ሀሰን ነዋሪነታቸው በደሴ ከተማ አስተዳደር ሰኞ ገበያ አካባቢ ነው፡፡ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ተሳትፈው የአካል
ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ማኀበሩ ተቋቁሞ ባደረገላቸው የገንዘብና የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ ከአባሎቻቸው ጋር በመሆን መሰረታዊ የፍጆታ
እቃዎችን እያከፋፈሉ በሚያገኙት ገቢ ራሳቸውን እየመሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ወይዘሮ ዘርፌ የተደረገው ድጋፍ ጥሩ ቢሆንም
ሌሎች በየጎዳናው የወደቁ የጦር ጉዳተኞች ድጋፍ ሊደረግላቸው እነደሚገባ ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ለሀገር መስዋእትነት የከፈሉ
የጦር ጉዳተኞችም የት ወደቃችሁ ሊባሉ ይገባል ብለዋል፡፡ ማኀበሩም ተጠናክሮ በመስራት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ሊያግዝ
እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች መርጃ ማኀበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉ ቢተውልኝ በአማራ ክልል ከ100 ሺህ በላይ የጦር
ጉዳተኞች ቢኖሩም በማኅበር የተደራጁት ከ18 ሺህ እንደማይበልጡ ተናግረዋል፡፡ እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ከእነዚህ የተደራጁ
የጦር ጉዳተኞች ውስጥ 215 ተመላሾች በወር 800 ብር የሚከፈላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው
ራሳቸውን እንደሚያሥተዳድሩ ገልጸዋል፡፡
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ማኀበሩ ከሰሜን ሸዋ፣ ከምስራቅ ጎጃም እና ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳር ዞኖች በስተቀር በሁሉም
በክልል ባሉ ዞኖች እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የማኀበሩ አባላት እንደጉዳታቸው መጠን ይሰሯቸዋል ተብለው በተጠኑ የሥራ
ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ቢሆንም ሁሉም ውጤት አምጥተዋል ማለት እንደማይቻልም ገልጸዋል፡፡
ማኅበሩ በማንኛውም ጊዜ በተካሄዱ ጦርነቶች ተሳትፈው ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ሳይለይ የሚያሣትፍ በመሆኑ ቁጥሩ
ከጊዜ ወደ ጊዜ እዬጨመረ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ መንግሥት ለሀገር
መስዋእትነት ለከፈሉ የጦር ጉዳተኞች ትኩረት ከሰጠ ቀጣይ የሚመጣውን የቤት ሥራውን እንደሠራ ይቆጠራል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኀላፊ እና የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ደሳለኝ ወዳጄ
የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች መርጃ ማኀበር ከህውሐት ጋር በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ በመሳተፍ አስተዋጽኦ
አበርክቷል ብለዋል፡፡ እነዚህን ጉዳተኞች ለማገዝ በተደረገው እንቅስቃሴ አንደ ጉዳት መጠናቸው በማደራጀት የሚንቀሳቀሱበት
መንገድ መመቻቸቱንም ተናግረዋል፡፡ አቶ ደሳለኝ ለአካል ጉዳተኞች እየተደረገ ያለው ድጋፍ አናሳ በመሆኑ መንግሥትና ማኀበሩ
ተጣምረው መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
7ኛ ጠቅላላ ጉባዓውን እያካሄደ ያለው የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች መርጃ ማኀበር በቀጣይ ሦስት ዓመታት ከመንግሥት ጋር
በመተባበር ማኅበሩን በማጠናከር አባላቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሠራ ከማኅበሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m




Previous articleበሲያትል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን አሜሪካ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በአግባቡ አንድትመለከት ጠየቁ፡፡

Source link

The post ለሀገር በከፈሉት ዋጋ ልክ ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ የአማራ ክልል የጦር ጉዳተኞች መርጃ ማኀበር አባላት ተናገሩ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

Trending Articles