Quantcast
Channel: The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

ʺፍቅርን በጀጎል ውስጥ አየኋት”|የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

$
0
0

ʺፍቅርን በጀጎል ውስጥ አየኋት”

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 18/2013 ዓ.ም (አብመድ) በዚያች ውብ ምድር ለምን መጣችሁ? እንዴት መጣችሁ? ከወዴት መጣችሁ? አይታወቅም፤ የሚታወቀው እንኳን ደህና መጣችሁ ነው፡፡ ፍቅርን ኖረዋለች፣ መቻቻልን አጊጣበታለች፤ አብሮነት ቀሚሷ፣ ፍቅር ትራሷ፣ ሰላም መቀነቷ አንድነት ውበቷ ነው፡፡

ʺየፍቅር ሀገር ነው የተወልድሽበት

ደግ ደግ ካፈራው ደስታ ከመላበት” እንዳለ ከያኒ ደግ ደግ ይወለድባታል፡፡ የፍቅር ዥረት ይፈስባታል፡፡ ከፍቅሯ ወንዝ ጠጥቶ፣ ከመቻቻሏ ባሕር ዋኝቶ ያልረካ የለም፡፡ ፍቅርን ስሟ አድርገዋለች፡፡ የምሥራቅ ደቡብ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ ፈር ቀዳጅ ይሏታል፡፡ የከተሜነት ምሳሌ፣ የንግድና የጥበብ፣ የባሕልና የታሪክ ባለቤትም ትባላለች፡፡

ቀደም ባለው ጊዜ በዚያ አካባቢ ሰባት መንደሮች ነበሩ፡፡ በሰባቱም መንደሮች የተለያዩ ጎሳዎች ይኖሩ ነበር፡፡ በሰባት መንደሮች የሰፈሩት ጎሳዎች በየጊዜው በጠላት ይጠቁ ነበር፡፡ ጠላት በሚመጣበት በኩል በመጀመሪያ የሚገኘው ጎሳም የከፋ ጥቃት ይደርሰበት ነበር፡፡ አንደኛው ለአንደኛው እስኪደርስ ድረስ ብዙ ጥቃት ይፈፀምበታል፡፡ ወረርሽኝና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችም ይደርሱባቸው ነበር፡፡ መከራው እየከፋ መጣ፡፡ መፍትሔ መፈለግ ግድ እያለ ሄደ፡፡ የሰባቱ መንደሮች ጎሳ መሪዎችና ሽማግሌዎች ተገናኙ፡፡ በችግራቸው ዙሪያም ተወያዩ፡፡

ʺከጥፋት የሚታደገን ቦታ ይኑረን፣ በአንድ ላይም እንሰባሰብ አሉ” ተስማሙም፡፡ ከሰባቱ መንደሮች የተሻለው እንዲመረጥ ተወሰነ፡፡ የተሻለ ሆኖ እንዲመረጥ ጠላት ሲመጣ ከሩቅ የሚታይበት፣ ጎርፍ የማያጠቃው፣ ወረርሽኝ የማይጠናበት፣ ወባ የማይኖርበት ሥፍራ መሆን ነበረበት፡፡ ከሰባቱም መንደሮች አንደኛዋ የተባለውን ሁሉ አሟላች፡፡ አስቀድሞ ሁሉን የተሰጣት ናትና በመራጮች ፊት ተመረጠች፡፡ በሰባቱ መንደሮች ሲኖሩ የነበሩ ጎሳዎችም በአንድ መንደር ውስጥ ተሰባሰቡ፡፡

የተመረጠችው መንደርም ʺኸንቲ ጌ” ትባል ነበር፡፡ ከተማም ሆና ተመረጠች፡፡ እነሆ ያቺ ከሰባት መንደሮች መካከል ምርጥ ሆና የተመረጠችው የዛሬዋ ሐረር ናት፡፡ ሐረር የሚለው ሥያሜም “ሐርላ” ከሚለው ነገድ የተወሰደ እንደሆነ የሐረሪ ክልል ባሕል ቅርስና ተሩዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና ታሪክ አዋቂው አዩብ አብዱላሂ ያስረዳሉ፡፡

በቀደመው ዘመን በዚያች ከተማ አስደናቂ ገበያ ነበራት፣ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የዓለም አቀፍ ሰዎችም ይገበያዩባት ነበር፡፡ ሐረር ለዘመናት ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ሆና ስትኖር ከመሃል ሀገር፣ ከአፍሪካ ቀንድ እና ከአረብ ሀገራት ጋር በንግድ ትገናኝ እንደነበር ይነገርላታል፡፡ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋርም በቀይ ባህር አማካኝነት ትገናኝ ነበር። የመቻቻልና የፍቅር ትምህርት ቤት፣ የአንድነት ሙዜም ናት እና ያያት ይወዳታል፣ ያላያት ያያት ዘንድ ይመኛታል፣ አይቷት የተመለሰው ሁሉ ሁልጊዜም ይናፍቃታል፡፡ አስቀድሞ ከተመረጡት የተመረጠች፣ ሁልጊዜም የተናፈቀች አድርጓታልና፡፡

በጎሳዎቹ ስምምነት የተመረጠችው መንደር የአሁኗ ታላቋ ሐረርን በዋናነት የመሠረቷት ሼህ አባድር እንደሆኑ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ታላቁ ሼህ አባድር ሐረርን ለ20 ዓመታት አስተዳድረዋል፡፡ በመካከልም ተሰወሩ፡፡ የሀገሬው ሰው ሼሃቸው ጠፍተዋልና ተጨነቀ፡፡ እንደ ዋዛም ዓመታት ነጎዱ፡፡ የሀገሬው ሕዝብ እኒያን ታላቅ ሰው እንደማይመለሱ እያሰበ ሄደ፡፡ ለ40 ዓመታትም ተሰውረው ኖሩ፡፡ ከ40 ዓመታት በኋላም 2 ዓመታት እንዳስተዳደሩ ታሪክ አዋቂው አዩብ ነግረውናል፡፡ በተሰወሩባቸው 40 ዓመታት ጊዜ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይታመናል፡፡ ሼህ አባድር በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍልም ደርሰው እንደነበር ይነገራል፡፡

በዚያች ከተማ ጦረኛው ኢማም አህመድ ኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (ግራኝ አህመድ) ነግሦባታል፡፡ ሐረር ሲጠራ ስማቸው የሚጠሩ ሌላኛው ታላቅ አሚር አሉ፡፡ እሳቸውም አሚር ኑር ይባላሉ፡፡ አመሪ ኑር ዲኒ ሙጃሂድ በሐረር ታላቅ ስም አላቸው፡፡ ሐረሪ ሲነሳ እሳቸው ሊረሱ አይችሉም፡፡ የሐረር ምልክቶች፣ ጌጦችና ሐብቶች የተሠሩት በእሳቸው ነውና፡፡ ዘመኑ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነው፡፡ የሐረር 42ኛው አሚር ነግሠው ነበር፡፡ ከሐረር ብሔራዊ ሙዜየም ያገኘሁት መረጃ በሐረር 72 አሚሮች መንገሳቸውን ያሳያል፡፡

42ኛው ንጉሥ አሚር ኑር የቀደመችውን ከተማና መናገሻቸውን የሚጠብቁበት ዘዴ ዘየዱ፡፡ ቀደምቷን ከተማ ዙሪያዋን ያሳጥሯት ዘንድ አሰቡ፡፡ ሥራቸውንም አስጀመሩ፡፡ በሦሥት ዓመታትም ያሰቡትን ፈፀሙ፡፡ ይህም ሥራ የዛሬዋ ሐረር መታወቂያ የጀጎል ግንብ ነው፡፡ ጀጎል ማለት አጥር ማለት ነው፡፡ አሚር ኑር የመናገሻ ከተማቸውን ከጠላት ለመከላከል ያስችላቸው ዘንድ ዙሪያውን ያሰሩት ግንብ ነው ጀጎል፤ ግንቡም አምስት በሮች አሉት፡፡ የበሮቹ ስያሜ ግንቡ ከመሠራቱ አስቀድሞ የነበረ የሰፈር ስም ነበር ነው ያሉኝ አዩብ፤ በሮቹም በሀደርኛ( በሐረርኛ) አርጎ በሪ፣ ስቁጣጥ በሪ፣ በድሪ በሪ፣ አሱም በሪና አስደኒን በሪ ይባላሉ፡፡

ጳውሎስ ኞኞ አጤ ምኒልክ በሚለው መፅሐፋቸው ሐረር ዙሪያዋን በግንብ ተከባ ወደ ከተማዋ የሚገባውም ከከተማዋ የሚወጣውም በአምስቱ በሮች ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ʺእነዚህም በሮች የተለያየ ስም ሲኖራቸው ታላቁ መግቢያ አስበዲን በር ይባላል፡፡ ይህ መድፍ ተጠምዶ የተቀመጠበት በር የጨርጨር ሰዎች መግቢያ ነው፡፡ ሁለተኛው ሱቅጣጥ በር ይባላል፡፡ ይህ በር ደግሞ የአርሲዎችና የጋራሙለታ ሰዎች የሚገቡበት ነው፡፡ ሦሥተኛው አርጎባ በር ይባላል፡፡ የፈዲሶች፣ የአርጎቦች፣ መግቢያ ነው፡፡ አራተኛው አሱም በር ይባላል፡፡ እሱም በር እንደ አስበዲን በር ሁሉ መድፍ የተጠመደበት ሲሆን የኢሶች መግቢያ ነው፡፡ አምስተኛው በር የሪር በር ይባላል፡፡ የየረሮች መግቢያ ነው፡፡ እነዚህ በሮች ሁልጊዜ በሚገባና በጥንቃቄ ይጠበቃሉ፡፡ ማታ ሲሆን በሮች ይቆለፉና የቁልፎቹ መፍቻዎች ለአሚሩ ይሰጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ነግቶ በሮቹ እስኪከፈቱ ድረስ የሚገባም ሆነ የሚወጣ የለም፡፡” ሲሉም በመፅሐፋቸው ያስረዳሉ፡፡

ጀጎል የነገሥታቱ መኖሪያ ግቢ ነው፡፡ በዚህ ግቢ ውስጥ 82 መስጂዶች፣ አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና አንድ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ይገኛሉ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ በጀጎል ውስጥ 90 መስጂዶች እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ 102 የቀብር ቦታዎችም በጀጎል ውስጥ ይገኛሉ።

በጀጎል ውስጥ ለውስጥ በተሠሩት ጎዳናዎች በቀስታ እያዘገምኩ ታላቅ ነገርን አየሁ፡፡ ጎደናዎቹ በፍቅር የተመሉ ናቸው፡፡ ፍቅርንም በጀጎል ውስጥ አየኋት፡፡ በዚያ ግቢ ውስጥ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባቶች በተመሳሳይ ጊዜ ለፈጣሪያቸው ምልጃ ያቀርባሉ፡፡ በአንድ አጥር ውስጥ የተለያየ ሃይማኖት፣ የተለያየ ጸሎት፣ የጠነከረ አንድነት ተመለከትኩ፡፡ ሦስቱም ፈጣሪያቸውን አብዝተው ይማፀናሉ፤ ስለሀገራቸውና ስለሕዝባቸው ሰላምን ይለምናሉ፤ ጀጎል ግንብ የተሠራበት ድንጋይ ራሱን ከአየር ንብረቱ ጋር እየለዋወጠ የሚኖር ድንቅ ጥበብ የታዬበት መሆኑም ተነግሮኛል፡፡ ሐረሪን የምትሞቅ ነገር ግን የማታቃጥል፣ የምትቀዘቅዝ ነገር ግን የማትበርድ ይሏታል- ውብ ናትና፡፡

ምኒልክ ኢትዮጵያ አንድ እንድትሆን እና በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት እንድትገዛ ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ ወደ ሐረር ዘመቱ፡፡ አስቀድመውም የያኔው የሐረር ገዢ የነበሩት አሚር አብዱላሂ እንዲገብሩላቸው ጠየቁ፡፡ አሚሩ ግን ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ አለመግባባቱ አድጎ ተጋጠሙ፡፡ አሚር አብዱላሂ ተሸንፈው ሐረር በምኒልክ እጅ ገባች፡፡ ምኒልክም ለተዋጓቸው ለአሚር ምህረት አድርገው እንዲገቡ አደረጉ፡፡ እርሳቸው ግን ሸሽተው ሄዱ፡፡ ሚኒሊክም ሐረር እንዲገብር አደረጉ፡፡ ሐገሪቱንም አደላደሉ፡፡ አስቀድሞ በዝናቸው ተሸብሮ የነበረው የሀገሬው ሰው ምኒልክን ቀርቦው ሲያያቸው ወደዳቸው፡፡ ምኒልክም ʺእኔ የእስልምናን ሐይማኖት ለማጥፋት አልመጣሁም፡፡ ሁሉም ሰው እንደየእምነቱ ያድራል” አሉ፡፡ ምኒልክ ሐረርን አደላድለው ሊመለሱ ሲሉ ʺከገበርንስ አትሂድብን ጠብቀን” አለ የሀገሬው ሰው፡፡ ምኒልክም አካባቢው እንዲጠበቅና እንዲቀና የውስጥ አስተዳደር ፈቅደው ተመለሱ፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊውና ታሪክ አዋቂው አዩብ ምኒልክ ለሐረር የውስጥ አስተዳደር በመስጠት ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው ነበር ያሉኝ፡፡ በዚያ ዘመን በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም ይሄን ያደረገ አልነበረምም ብለውኛል፡፡ በእርግጥ ምኒልክ ለሐረር ብቻ ሳይሆን ለሌሎች አካባቢዎችም የውስጥ አስተዳደር ፈቅደዋል፡፡ ምኒልክ በሐረር አሚር ሾመው ነበር የተመለሱት፡፡ የሾሟቸው አሚርም አሊ አቡበክር ይባላሉ፡፡ አሊ አቡበክር የአሚር አብዱላሂ አጎት መሆናቸውን ጳውሎስ ኞኞ ጽፈዋል፡፡ አጤ ምኒልክ የሐረርን ሕዝብ በሚገባ ያውቁታል ብለውኛል አቶ አዩብ፡፡ ምኒልክ አፍሪካ በጨለማ ዘመን በነበረችበት ወቅት የውስጥ አስተዳደር የፈቀዱ አስታዋይና ብልህ መሪ ናቸው፤ ባለውለታም ናቸው ነው ያሉኝ፡፡ ሐረር በዓድዋ ጊዜ በራስ መኮንን እየተመራ የተሻለ ትጥቅና ስንቅ ይዞ ዘምቷል፡፡ ድልም አድርጎ ተመልሷል፡፡

ሐረር በሀብቷ፣ በመቻቻል፣ በፍቅር፣ ኢትዮጵያን በመገንባት ባደረገችው አስተዋፆዖ የኢትዮጵያ ውብ ጸጋ ናት ይሏታል፡፡ በሐረር የነበሩት አሚሮች መኖሪያቸው በጀጎል ግቢ ውስጥ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡ የሐረር አሚሮች እንደ ዜጋው እንጂ እንደ ንጉሥ ድሎትን የማይመኙ ለሕዝብ ቅርብ የሆኑ ነበሩ፡፡ በሐረር ከተማ ከጀጎል ግንብ ወጥቶ በሰፊው ቤት መሠራት የተጀመረው በጣልያን ወረራ ጊዜ እንደነበር ይነገራል፡፡

ቀደም ባለው ጊዜ ለከተማዋ አስፈላጊ ናቸው የተባሉት ሁሉ የሚሠሩት በጀጎል ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ በዚያ ዘመን ጀጎል ሥራም፣ መዝናኛም መኖሪያም ነበር፡፡ ሐረሪዎች ቡናን ከጫካ አውጥቶ ተወዳጅ በማድረግ የሚቀድማቸው እንደሌለም አዩብ ነግረውኛል፡፡ በሐረሪ ቡና እንደማንኛውም አካባቢ ተቆልቶ ይጠጣል፡፡ “ቁጢቃላ” የሚባለው ተደርቆ ከወተት ጋር ይጠጣል፡፡ “ቁጢቃላ” ማለት የቡና ቅጠል ማድረቂያ ማለት ነው፡፡ የቡናው ገለፈቱም ተፈልቶ እንደሻይ ቅጠል ከወተት ጋር ይጠጣል፡፡ ፍሬ ያልያዘ ቡና ከቂቤ ጋር ተቀቅሎ “ስሪ” ከተባለ ዳቦ መሰል ጋር ይበላል፡፡

ጀጎል ውስጥ ሁሉም አለ፡፡ ጀጎል ውስጥ ኢትዮጵያ አለች፡፡ የኢትዮጵያን መልክ፣ የኢትዮጵያን ባሕሪ ማየት ይቻላል፡፡ ሐረሪ ውስጥ በአንድ ሰርግ በተለያየ ቋንቋ ይጨፈራል፡፡ በአንድም ለቅሶ በተለያየ ቋንቋ ይለቃሳል፡፡ ሐረር ውስጥ ንግግር በየትኛው ቋንቋ ተጀምሮ በየትኛው ቋንቋ እንደተጨረሰ የሚያስታውስ የለም፡፡ መግባባታቸው ከአንደበት ሳይሆን ከአንጄት ነውና በተገኘው ጭውውቱ ይደራል፡፡ መታደል ነው፡፡

ሐረርን የማይናፍቅ ያለ አይመስልም፡፡ ሐረር ስትነሳ ፍቅርና መቻቻል ትዝ ይላል፡፡ እኔም እድል ገጥሞኝ የተመኘሁትን አየሁት፤ ሐረሪ በብዙ ነገር ብትታወቅም የበለጠ ለማስተዋወቅ ሙዜዬሞችን የመክፈትና ሌሎች ሥራዎችን የማከናወን እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውንም ሰምቻለሁ፡፡ የሀገር ውስጥ የፍቅርና የእህትማማቾች ከተሞች እንዲበዙ እየሰሩ መሆናቸውንም ነግረውናል፡፡

ሐረር ውስጥ እንግዳ የሚባል ነገር የለም፡፡ ፍቅራቸው በቶሎ ያለምዳል፤ ባይተዋር አያደርግም፤ አዎን አንቺ ሱስ የሆንሽ ከተማ ከፍቅርሽ ወንዝ ጠጣሁ፤ ከመቻቻል ባሕርሽ ዋኘሁ፤ ባደረግሽልኝ ነገርም ረካሁ፤ ደስም አለኝ፤ በተቀደሰችው ቦታ የተቀደሰ ሕዝብ አለና ሰላምና ፍቅራቸው ለዘለዓለም እንደዥረት ሲፈስ ይኖር ዘንድ ተመኘሁ፡፡ መልካም ናችሁና መልካሙን ሁሉ ለእናንተ ተመኘሁ፡፡

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post ʺፍቅርን በጀጎል ውስጥ አየኋት” | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

Trending Articles