
ሱማሌ ክልልን ለሁሉም ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያውያን መልከ ብዙና ቀለመ ዥንጉርጉር የሆንን፣ ኅብረ ብሔራዊነት የተላበስን፣ የባህል፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የመልክአ ምድር ብዝሃነትን የተቸርን ሕዝቦች ነን፡፡ በቁጥርም 100 ሚሊዮኖችን የተሻገረን ትልቅ ሀገር ሆነን ሳለ የተበላሸ የፖለቲካ ስሪትን ተከትሎ ሺህ ዓመታትን የተሻገረው አብሮነት ተሸርሸሮ ወንድም በወንድሙ ላይ ሞትን ፈርዷል፡፡
ለዚህ ደግሞ የትናንት የኛ የሆነው የጋራ ታሪክ መዛባት እና የጋራ እውነታዎች መካድ በምክንያትነት ይነሳል፡፡ ችግሩ ደግሞ በአራቱም የሀገሪቱ ጫፍ መሆኑ አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡
በሱማሌ ክልልም የነበረው ይህ ነው፡፡ በጅግጅጋ ከተማ ያነጋገርናቸው ሙሉቀን የስጋትና ሰይድ ሰይፉ ከስምንት ዓመታት በፊት ከአማራ እና ከደቡብ ክልል ለሥራ እንደመጡ ነግረውናል፡፡ ከለውጡ አመራር በፊት ሠርቶ ለማደር፣ በፍትሕ ተቋማት እኩል ለመዳኘት፣ በተቋማት ተቀጥሮ ለመሥራትም ሆነ በነጻነት ለመንቀሳቀስ ሁኔታዎች አስቸጋሪ እንደነበሩ አንስተዋል፡፡
አሁን ግን በመጣው ለውጥ ነገሮች በሂደት እየተለወጡ በእኩልነት መኖር መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በሱማሌ ክልል የነበረው አመራር ካለፈው 2010 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በኅይል ተወግዶ አዲሱ አመራር ክልሉን ለመምራት ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ ሠላምና አብሮነት ተረጋግጦ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መብቱ ተክበሮ ሀብት ማፍራት ጀምሯል ነው ያሉት፡፡
“የሰው ልጅ እኩል ነው፤ ማንም መርጦ አልተወለደም” በማለት አብሮነትን በየመድረኩ መስበክ ብቻ ሳይሆን በተግባር ያረጋገጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ እና በስራቸው ያሉ የሥራ ኀላፊዎች ሀሳቡን መግዛት ለለውጡ መሰረት ሆኗል ሲሉም ተናግረዋል ነዋሪዎቹ፡፡
በሱማሌ ክልል ጊዜያዊ የሠላምና የፍትሕ ማኅበር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቶ ደረጀ አስፋው በክልሉ የነበረው ሕዝብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዳይሆን እና የፖለቲካ ውክልና እንዳያገኝ ተቋማዊ በሆነ መልኩ ሲሠራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
እንደ ሀገር የተበላሸው ፖለቲካ በአንድ ብሔር ላይ ይሠራ የነበረው የተዛባ ትርክት ዋጋ ሲያስከፍል መቆየቱንም ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን ነገሮች በሂደት እየተስተካከሉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሚያጋጥማቸው ጫናም ካለ ሌሎች ምክክር የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ሲገጥሙ በቀጥታ የክልሉን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች በማግኘት ለችግሮች ምላሽ እየተገኘ ነው ብለዋል፡፡
ሕዝብ ለሕዝብ ውይይት በማካሄድም ማንኛውም ሰው በክልሉ የመኖር፣ ሰርቶ የመለወጥና በነጻነት የመንቀሳቀስ ያልገደብ መብት አለው በሚለው ጉዳይ ሙሉ መግባባት በሥራ ኀላፊዎች እና በሕዝቡ መካከል መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡ ከታች እስከ ላይ ያለው የሥራ ኀላፊ ይህን በመተግበሩ አሁን ላይ በሱማሌ ክልል ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ እና በአብሮነት እየኖሩ ነው ያሉት የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ምክትል ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ሙሐመድ ሮብሌ ናቸው፡፡
በተለይ በሥራ ኀላፊዎች እና በጸጥታ አካሉ በኩል የተሠራው ሥራ ጠንካራ በመሆኑ ክልሉ ላይ በአሁኑ ወቅት ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች በተሻለ ሠላም ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በቀጣይም ለሁሉም ተምሳሌት የሆነ ክልል ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ እየተሠራ መሆኑን አቶ ሙሐመድ በተለይ ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ጋሻው ፈንታሁን
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post ሱማሌ ክልልን ለሁሉም ተምሳሌት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.