በግብር እና ታክስ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ የአሠራር መመሪያዎችን ተከታትሎ ለንግዱ ማኅበረሰብ ማሳወቅ እንደሚገባ የፌደራል ግብር ከፋዮች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 17/2013 ዓ.ም (አብመድ) በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአገልግሎት አሰጣጡን በሚመለከት ከግብር ከፋዮች እና አጋር አካላት ጋር ለሁለት ቀናት የዘለቀ ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
የውይይቱ ዓላማ በገቢ ሰብሳቢው ተቋም እና በግብር ከፋዩ መካከል ያሉ የአሠራር ክፍተቶችን ግብዓት በመውሰድ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ለማሻሻል ያለመ መሆኑን የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን ደመመ ገልጸዋል፡፡ “ግብር እና ታክስ ለሀገር ልማት የሚከፈል ዋጋ ነው” ብለዋል አቶ ካሳሁን፡፡ በታማኝነት እና በፈቃደኝነት ግብር እና ታክስ የመክፈል ጠንካራ ባህል የገነባ ማኅበረሰብ ለመፍጠር መሰል ግንኙነቶች ቀጣይነት ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
በዲጂታል ሥርዓት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም የሚስተዋለውን መጉላላት መቀነስ እንደሚገባም ከአማራ ፕላስቲክ ፋብሪካ የመጡት አቶ ወንዳለ ዋሴ ጠቁመዋል፡፡ የባለሙያዎች ቀናነት እና ሥራን በስልክ እና በአካል ለመደገፍ ያለው ቁርጠኝነት መልካም እንደሆነም አስተያየት ሰጭው ጠቅሰዋል፡፡ በሠራተኞች መካከል ያለውን የአቅም ልዩነት ለማጥበብ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
በዲጂታል ሥርዓቱ ላይ ያሉ ችግሮች መሰረታዊ ሆኗል ያለችን ከኩሪፍቱ ሆቴሎች ድርጅት የመጣችው ሠላማዊት መኳንንት በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ የአሠራር መመሪያዎችን ተከታትሎ ለንግዱ ማኅበረሰብ በማድረስ በኩልም ክፍተቶች እንደሚስተዋሉ ጠቅሳለች፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ተከታታይ ድጋፍ እና ክትትል ያስፈልጋልም ብላለች፡፡
የአሠራር መመሪያዎችን ለማስተዋወቅ እና ግንዛቤ ለመፍጠር የንግዱ ማኅበበረሰብ ለውይይት ሲጠራ የመምጣት ችግር እንደሚስተዋል አቶ ካሳሁን አንስተዋል፡፡ በግብር ከፋዮቹ የተነሱት ውስንነቶች ግን የሉም አይባልም ነው ያሉት፡፡
• በባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት 4 ሺህ 370 በላይ የንግድ ፈቃድ ምዝገባ ተካሂዷል፡፡ ከእነዚህ መካከል 2 ሺህ 225 የሚሆኑ የንግድ ተቋማት በግብር እና ታክስ ክፍያ ላይ ይገኛሉ፡፡
• ባለፉት ስምንት ወራት 116 የታክስ ውሳኔዎች ቅሬታ ቀርበው ለ100 ቅሬታዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ 63ቱ ቅሬታዎች ፀንተዋል፤ 18ቱ ተሻሽለዋል፤ 12ቱ ተሽረዋል፤ 5 ቅሬታዎች በቅሬታ አቅራቢዎች ተነስተዋል፤ 2 ቅሬታዎች በአግባቡ ያልቀረቡ ቅሬታዎች በሚል ተመልሰዋል፤ እንዲሁም ቀሪዎቹ 16 ቅሬታዎችን ለማየት በሂደት ላይ ነው፡፡
• ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት 3 ነጥብ 86 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ የዕቅዱን 67 ነጥብ 29 በመቶ ወይም 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል፡፡
• ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በ2013 በጀት ዓመት 290 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ባለፉት ስምንት ወራት 191 ነጥብ 45 ቢሊዮን ብር ሰብስቧል፡፡
• በገቢዎች ሚኒስቴር ደረጃ በፌዴሬሽን የ50 በመቶ የገቢ ትልልፍ ቀመር መሰረት ባለፉት ስምንት ወራት ከተሰበሰበው ገቢ ውስጥ 3 ነጥብ 03 ቢሊዮን ብር ለአማራ ክልል ገቢ ተደርጓል ተብሏል፡፡
• በፌደራል ገቢዎች ሚኒስቴር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከአክሲዮን ማኅበራት፣ ኀላፊነታቸው ከተወሰነ የግል ማኅበራት፣ ጥቃቅን ካልሆኑ በስተቀር የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የኅብረት ሽርክና ማኅበራት፣ በፌደራል ከተቋቋሙ የልማት ድርጅቶች እና ከፌደራል ተቋማት ገቢ ይሰበስባል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post በግብር እና ታክስ ዙሪያ በየጊዜው የሚወጡ አዳዲስ የአሠራር መመሪያዎችን ተከታትሎ ለንግዱ ማኅበረሰብ ማሳወቅ እንደሚገባ የፌደራል ግብር ከፋዮች ተናገሩ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.