የአማራ ልዩ ኃይልን በተሳሳተ መንገድ መተቸቱና መኮነኑ መሰረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2013 ዓ.ም (አብመድ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው “ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” በሚለው ሀገራዊ ብሂል ነው መልእክታቸውን የጀመሩት፡፡
ዋና አስተዳዳሪው የጁንታው የትህነግ ቡድን በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ሲፈፅም በመንግሥት የተሰጠውን ሀገር የማዳን ተልዕኮ በሙሉ እምነት ተቀብሎ ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጎን በግንባር ቀደምነት የቆመው የአማራ ልዩ ኃይል ነው ብለዋል። ይህ ደግሞ ማንም ሊክደው የማይችል ትልቅ ሀቅ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ ሕግ ማስከበሩ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባርና እሴት የጠላት ኀይል ቁስለኛን እያከመ፣ የተማረከን በክብር እየተቀበለ፣ የራሱን ስንቅ እያጎረሰና ውኃ እያጠጣ ለሌላ ድል እየተዘጋጀ ለመሄዱ በተለያዩ የጦርነት ቦታዎች የተማረኩና የቆሰሉ የጁንታው ወታደሮች ምስክሮች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ዋና አስተዳዳሪው እንዲህ ከፍተኛ ጀብድ ለሠራ የአማራ ልዩ ኃይል ምሥጋናና እውቅና ሊሰጠው ሲገባ በአንዳንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለምንግዜም የአማራ እና የኢትዮጵያ ጠላት ለሆኑት ለተደመሰሰው የጁንታው ኃይልና ለኦነግ ሸኔ ማይክ ለመሆን የአማራ ልዩ ኃይልን በተሳሳተ መንገድ መተቸቱና መኮነኑ መሰረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ ደሳለኝ ጣሰው የአማራ ልዩ ኃይል አሁንም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን ዛሬም በርሃ ለበርሃ ዳር ድንበር እያስከበረ ይገኛል ብለዋል።
እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ሁለት የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ያነሱት መሠረተ ቢስ ትችትና ወቀሳ የትህነግ ጁንታ ፍርስራሽ ኃይል እኩይ ዓላማ ሠለባ ስለመሆናቸው ትልቅ ማሳያ እንደሆነ ነው የጠቀሱት።
ስለሆነም የሰጡት አስተያየት የተጨበጠ መረጃ የሌለውና የአስተያየቱ አቀራረብ የምክር ቤቱን ክብር ያልጠበቀ በመሆኑ በምክር ቤቱ ደንብ እና አሠራር መሰረት ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል። ምንጭ፡-የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
The post የአማራ ልዩ ኃይልን በተሳሳተ መንገድ መተቸቱና መኮነኑ መሰረተ ቢስና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.