Quantcast
Channel: The Habesha: Latest Ethiopian News, Analysis and Articles
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ማደጉ ኅላፊነቱን በላቀ ብቃት ለመፈጸም እንደሚያስችለው ምሁራን ተናገሩ፡፡

$
0
0

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ማደጉ ኅላፊነቱን በላቀ ብቃት ለመፈጸም እንደሚያስችለው ምሁራን ተናገሩ፡፡

ባሕር ዳር: መጋቢት 10/2013 ዓ.ም (አብመድ) የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ማደጉ ለተቋማዊ ነፃነት፣ ገለልተኛነት እና ለሙያዊ ነፃነት በር እንደሚከፍትለት አሚኮ ያነጋገራቸው የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት ምሁር ተናግረዋል፡፡

በህትመቱ ዘርፍ የክልሉ ፋና ወጊ ጋዜጣ ‹‹በኩር›› ብቸኛ የክልሉ መውጫ ልሳን ነበረች፡፡ 1995 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 88/95 የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወይም የአማራ ማስሚዲያ ኤጀንሲ በሚል ስያሜ ሕጋዊ ሰውነት ከማግኘቱ በፊትም በራዲዮ ስርጭት እና ቴሌቪዥን ዘርፍ ወኪል ሆኖ አገልግሏል፡፡ በጊዜ ሂደት ራሱን ከወቅት ጋር እያናበበ እና እያደገ የመጣው የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ዛሬ ላይ ከስድስት በላይ የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎች፣ በርካታ የማቀባበያ ጣቢያዎች፣ በሦስት ቋንቋ ለህትመት የሚበቁ ጋዜጦች እና የዓለም አቀፍ ተደራሲ ባለቤት ሆኗል፡፡

ስያሜውም አገልግሎቱን እና የተደራሽነት አድማሱን በሚመጥን ልክ ከሰሞኑ ‹‹የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን›› ወደ ሚል ቀይሯል፡፡ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የድርጅቱ ጉዞ ከውጭም፣ ከውስጥም፣ ከጊዜም፣ ከአቅምም ጋር የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ የሕዝብ ድምፅ በመሆን ሰርቷል ያሉን የደሴ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በየነ ፈንታው ናቸው፡፡

በየጊዜው የሚፈጠረው ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ዳፋ አንድ ወቅት ጎላ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ቢያደርጉትም ‹‹የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የክልሉን ሕዝብ እሴቶች እና የፖለቲካ ሚዛን በማስጠበቅ የጎላ ድርሻ ነበረው›› ነው ያሉት፡፡ ወደ ኮርፖሬሽን ማደጉም ኅላፊነቱን በላቀ ብቃት እና ወጥ በሆነ ሂደት እንዲፈፅም እንደሚያስችለው ተናግረል፡፡

የተጠሪነት ለውጥ፣ በስሩ የያዛቸው ድርጅቶች ብዛት፣ የተደራሽነት ስፋት፣ ገቢ የማመንጨት ፍላጎት እና የቀጣይ ጊዜ ራዕይ ኮርፖሬሽን የሚለውን ስያሜ ማግኘት ግድ ብሎት ነበር ያሉን ደግሞ የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት የሕግ ባለሙያ አቶ በጊዜው ገነት ናቸው፡፡

የእንግሊዝኛው ስያሜው ‹‹ኤጀንሲ›› እና የአማርኛ ስያሜው ‹‹ድርጅት›› ሁለት የተለያዩ መዋቅሮች ስያሜ ለአንድ ተቋም መሰጠቱም ለመዋቅራዊ ለውጡ አንድ ምክንያት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የተደራሽነት አድማሱን ለማስፋት፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የዜና ወኪሎችን ለማሰማራት እና ጽሕፈት ቤቶችን ለመክፈት እንዲሁም ጊዜው የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ ለመጠቀም እና ገቢ የመሰብሰብ አቅሙን ለማሳደግ አዲስ መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገው ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በዘፈቀደ ይፈፀሙ የነበሩ ተግባራትን ሕጋዊ ለማድረግ፣ ሙያዊ ተጠያቂነትን እና ነፃነትን ለማስፈን ኮርፖሬሽን መሆኑ አስፈላጊ መሆኑን ነው የሕግ ባለሙያው የገለፁት፡፡ ስያሜውን የሚመጥን፣ በክልሉ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተመራጭ ሚዲያ ለመሆን እየሠራ እንደሆነ የሕግ ባለሙያው አብራርተዋል፡፡ በሂደት የስርጭት አድማሱን እና የተደራሽነት መጠኑን እያሰፋ እንደሚሄድም አስታውቀዋል፡፡

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህሩ እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዲግሪ ተማሪው አየለ አዲስ “የቀድሞው የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ማደጉ ከአገልግሎት ሰጭነት ወደ ሚዲያ ኢንዱስትሪነት ያሸጋግረዋል፤” ብለዋል፡፡ ይህም ለዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት፣ ለተቋማዊ ነፃነት፣ ገለልተኛነት እና ሙያዊ ነፃነት እንደሚያጎናጽፈው ነው ያስረዱት፡፡ ድርጅቱ ወደ ኮርፖሬሽን ሲያድግ ገቢ የማመንጨት አቅሙ ስለሚያድግ በክልሉ ውስጥ አማራጭ የሚዲያ ተቋማት እንዲያድጉ ለመደገፍ እና ቅርንጫፎቹን ለማስፋት እድል እንደሚኖረውም መምህሩ ተናግረዋል፡፡

በጀት ቢዘገይ በአማራጭ የፋይናንስ ምንጮች ሥራ ሳይጓተት ለመሥራት እንደሚያግዘውም ጠቅሰዋል፡፡ ለይዘት ቀረፃ ዓለም ዓቀፋዊነትና ከባቢያዊነት፣ ከዘመን ጋር ለመዘመን፣ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለመጠቀም እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማለም እንደሚረዳውም ነው መምህር አየለ የተናገሩት፡፡

እንደ መምህር አየለ እይታ ድርጅቱ ኮርፖሬሽን ሲሆን የላቀ ኀላፊነት፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነት እና ሙያዊ ክህሎት በእጅጉ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም እንዲረዳው ተቋማዊ ገለልተኛነት ላይ ከጽንሰ ሃሳብ በዘለለ የአሠራር ስርዓት መዘርጋት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬት ማደግ ተገቢ እና ወቅታዊ እንደሆነም አቶ በየነ ፈንታው ተናግረዋል፡፡ “የክልሉ ሕዝብ በበሬ ማረስን ለዓለም አስተዋውቆ እስካሁንም በበሬ ያርሳል፤ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ሀገር ያቆመ ሕዝብ በሃሰት ትርክት ዋጋ እንዲከፍል ሆኗል፤ እንዲሁም የክልሉ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች አደጋ እየተጋረጠባቸው ነው” ብለዋል፡፡

ግብርናን ማዘመን፣ ምጣኔ ሃብቱ እንዲያንሰራራ መሥራት፣ የፖለቲካ ኀሎችን የኀይል አሰላለፍ መተንተን፣ የሕዝቡን ስነ ልቦና መጠገን እና የተሳሳቱ ትርክቶችን ማረም ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሚጠበቁበት የቀጣይ ጊዜ ኀላፊነቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ወደ ኮርፖሬሽን ማደጉ ኅላፊነቱን በላቀ ብቃት ለመፈጸም እንደሚያስችለው ምሁራን ተናገሩ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13041

Trending Articles