
ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብን ለውስጥ የፖለቲካ ችግሮቻቸው መፍትሔ ለማድረግ እየጣሩ እንደሚገኙ ምሁራን ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) ግብጽና ሱዳን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የውስጥ ፖለቲካ
ችግሮቻቸው የመፍትሔ ቁልፍና ማረጋጊያ ለማድርግ እየጣሩ መሆኑን ምሁራን ተናገሩ።
ኢትዮጵያውያን የግድቡን ግንባታ በፍጥነት በማጠናቀቅ ሀገር ወዳድነታቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባቸውም ተጠቁሟል።
የጥቁር አባይ መነሻ የሆነችውና የዓባይ ውኃ 86 በመቶ አመንጪ ኢትዮጵያ ብትሆንም ወንዙ ድንበር ተሻግሮ የግብጽና ሱዳንን
የኤሌክትሪክ ኃይልና የእርሻ ፍላጎት ሲያሟላ ለዘመናት ቆይቷል።
በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1929 እንዲሁም በ1959 ግብጽና ሱዳን ውኃውን በብቸኝነት መጠቀም የሚያስችላቸውን የቅኝ
ግዛት ስምምነት አድርገዋል።
ሁለቱ ሀገሮች አሁንም ድረስ ይህ ውል ተግባራዊ እንዲሆንና ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃን ተጠቅማ ምንም አይነት የልማት ሥራዎችን
እንዳታከናውን ያላቸውን ፍላጎት በግልጽ እያሳዩ ይገኛሉ። ለአብነትም ግብጻውያን በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሠሩ
ባለሙያዎቻቸውን በመጠቀም ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃን ተጠቅማ ማንኛውንም መሰረተ ልማት ማከናወን የሚያስችላትን የገንዘብ
ድጋፍ እንዳታገኝ ብዙ ሠርተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዲፕሎማሲና የታሪክ ምሁራን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተሻለ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖራትም ሃብቱን
እስካሁን ጥቅም ላይ ባለማዋሏ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በድህነትና በኋላቀርነት እንድትነሳ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ የውኃ ሃብቷን ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሏ የበይ ተመልካች ሆና መቆየቷን ምሁራኑ አንስተዋል።
የዲፕሎማሲና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳለ ንጉሴ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የያዘችው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ
በግብጽና ሱዳን ዘንድ ተቀባይነት ያላገኘበት ዋነኛ ምክንያት ሀገሮቹ የቅኝ ግዛት አመለካከታቸው ባለመቀየሩ ነው። ሀገሮቹ
ከአፍሪካ አልፎ የተለያዩ ዓለም ሀገሮች ጉዳዩን ወስደው መፍትሔ ፍለጋ የመኳተናቸው ምክንያትም የአስተሳሰባቸው ውጤት
መሆኑም እንዲሁ።
እኤአ በ2015 ሦስቱ ሀገሮች በመሪዎቻቸው በኩል ከተፈረመ ስምምነት ውጭ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ጉዳይ ምንም አይነት ውል
እንዳልፈረመች ገልጸው፤ “በዚህ ስምምነት ሀገሪቷ በተፈጥሮ ሃብቷ መልማት እንደምትችል ግብጽና ሱዳን ዕውቅና ሰጥተዋል”
ብለዋል።
የታሪክ ተመራማሪና መምህሩ ዶክተር አልማው ክፍሌ፤ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከዲዛይኑ ጀምሮ እስከ ገንዘብ ምንጩ
በኢትዮጵያውያን መከወኑ የአሁኑ ትውልድ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤትነቱን ያስቀጠለበት መሆኑን ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ከጀመረች ጀምሮ በግብጽና በሱዳን ይደርስባት የነበረውን ጫና ተቋቁማ በተፈጥሮ ሃብቷ መጠቀም
እንደምትችል የመጀመሪያውን ውኃ መሙላቷ በቂ ማሳያ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አቋም ከአፍሪካውያን አልፎ ለዓለም ትልቅ ትምህርት የሰጠና ለአፍሪካዊያን ይሰጥ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት
የቀየረ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና ኦሬንታል ጥናትና ምርምር ተቋም መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ በበኩላቸው
ግብጽና ሱዳን የዓባይ ውኃን የልማት ሳይሆን የፖለቲካ ጉዳይ በማድረግ ዓለምአቀፋዊ ትኩረት ለመሳብ እየሞከሩ ነው። “ይሁንና
ኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር የዓባይ ውኃን ተጠቅማ የመልማት መብቷን የመንፈግ ምኞታቸው አይሳካም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት የሚያደርጉትን የሦስትዮሽ ድርድር መቋጫው አፍሪካ ሕብረት መሆኑንም
በመግለጽ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በግድቡ ጉዳይ ለረጅም ዓመታት ሲደራደሩ የነበሩት አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስና ዶክተር
አልማው ክፍሌ እንደሚሉት፤ ግብጽም ሆነች ሱዳን የግድቡን ጉዳይ የውስጥ ፖለቲካ ችግሮቻቸውን ለማረጋጋት እየተጠቀሙበት
ነው ብለዋል።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ የልማት ጥያቄውን ለመመለስ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን በመረዳት ከልዩነት ይልቅ
አንድነትን በማጠናከር የግድቡን ግንባታ ከዳር በማድረስ ኀላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
አጠቃላይ የግንባታው ሂደት 79 በመቶ የደረሰውን ግድብ ቀሪ ሽራዎች ለማጠናቀቅ እያንዳንዱ ዜጋ የሚያደርገውን ተሳትፎ
በማጠናከር ኀገር ወዳድነቱን በተግባር እንዲያሳይ ምሁራኑ ጥሪ አቅርበዋል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
The post ግብጽና ሱዳን የህዳሴ ግድብን ለውስጥ የፖለቲካ ችግሮቻቸው መፍትሔ ለማድረግ እየጣሩ እንደሚገኙ ምሁራን ገለጹ፡፡ first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.