
“ሩጫው የተገታው ባቡር”
ባሕር ዳር፡ መጋቢት 09/2013 ዓ.ም (አብመድ) በአዕምሮው የሚሮጥ መሪ በምድር የሚሮጥ ሥራ ሰርቶ ያሳያል፤ ከመናገሩ በፊት ያስባል፤ በጥንቃቄ ይናገራል፤ የተናረውን ይፈፅማል፤ ምኒልክ በሀሳብም በተግባርም ሮጦ የቀደመ መሪ ነው፡፡ ታላቅ ነገር ያስባል፤ ይፈፀምለት ዘንድ ፈጣሪውን ይማፀናል፤ ፈፅሞም ያሳያል፡፡ የሀገሬው ሕዝብ ጉዞው በፈረስ፣ በበቅሎና በግመል ነበር፡፡ በጉዞው እሾህና አሜኬላው፣ ረሃብና ጥሙ አያድርስ ነበር፡፡ በዘመኑም ኢትዮጵያዊያን ሕይወታቸውን ቀለል የሚያደርግ ነገር ይሹ ነበር፡፡ ይህን የሚያደርግ መሪም እንዲመጣላቸው አጥብቀው ይመኙ ነበር፡፡
ምኒልክ ነገሠ፡፡ ሌላ የስልጣኔ ዘመንም ደረሰ፡፡ ታላቁ ንጉሥ ሀገሩ ኢትዮጵያ ከስልጣኔ ላይ ስልጣኔ ትጨምር ዘንድ አብዝቶ ይሻል፡፡ ይህን ያደርግ ዘንድ ተነሳ፡፡ አያሌ ነገሮችንም አደረገ፡፡ ምኒልክ ባሠራውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በመሆነው ባቡር ጣቢያ ውስጥ ተገኝቻለሁ፡፡ ይህም የድሬዳዋ ምድር ባቡር ነው፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ድርጅት ይባል ነበር፡፡ ቆይቶም የፈረንሳይ መንግሥት በግንባታው ይሳተፍ ስለነበር የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ምድር ባቡር ድርጅት ተባለ፡፡ ከጊዜ በኋላ ጅቡቲ ነፃ ሀገር ስትሆን የኢትዮ -ጂቡቲ የምድር ባቡር ድርጅት ተባለ፡፡
ከጊዜ በኋላም ኃይለ ሥላሴ በሠሩት ሥራ ፈርንሳይ የነበረው ዋና መሥሪያ ቤቱ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣና የኢትዮጵያ ጥቅምም ከፍ እንዲል ተደረገ፡፡ ድሬዳዋ ስትነሳ ባቡር አብሮ ይነሳል፡፡ ድሬዳዋን ያለ ባቡር ማሰብ የሚቻል አይመስልም፤ የዘመናዊነቷ፣ የፍቅሯና የእድገቷ መሠረት ባቡር ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ድሬዳዋ በየቀኑ እንግዳ ተቀባይ ናት፡፡ ለዚያውም በሺህዎች የሚቆጠሩ እንግዶችን፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገቡ እንግዶችም ድሬን በፍቅርና በሕብረት ያደምቋታል፡፡
አሁን ላይ ግን እንግዶች የናፈቋት ይመስላሉ፡፡ የባቡር ጣብያውን ተዘዋውሬ ተመለከትኩ፤ ዝምታን የመረጠ ይመስላል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ወጭና ገቢ የለም፡፡ ማሽኖችና ጋሪዎች ቆመዋል፡፡ መሥራት እየቻለ የተከለከለ ይመስላል፡፡ ለምን?
የድሬዳዋ ምድር ባቡር የማሽን ሾፕ ኃላፊ ሚናስ በቀለ ምድር ባቡሩ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ማሽኖች ያሉትና አሁንም በጥራት የሚሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ የምድር ባቡሩ ጥራት ያለውና ኀላፊነት የሚሰማው ሠራተኛም አለው፡፡ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረው ማሽን እና የካበተ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የማሽን ጥገና ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸውን ድርጅቶች በብቃት እንደሚደግፉም ነግረውናል፡፡
ኢትዮጵያ ለምታስገነባቸው የባቡር መስመሮችም ሊኖር የሚችለውን የእውቀት ክፍተት መሙላት የሚችሉ ባለሙያዎች ያሉበት ተቋምም ነው፡፡ ታዲያ ለምን ሥራው ቀዘቀዘ? ባቡሩ ትኩረት ተነፈገውና በእርሱ ምትክ መኪናዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ባቡሩ ከወደብ የሚያርፉ ጥሬ እቃዎችን ማቅረብ ሲችል ባቡሩ ቆሞ መኪናዎች በወደብ የሚገቡ ጥሬ እቃዎችን እንዲያመጡ ተደረገ፡፡ ባቡሩ በሙሉ አቅሙ በሚሠራበት ጊዜ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ በየመዳረሻቸው በርካታ ሠራተኞችን ይቀጥራሉ፡፡ ነጋዴዎች ነግደው ያተርፋሉ፤ በሥራቸውም ብዙዎችን የሥራ እድል ተጠቃሚ ያደርጋሉ፡፡
የባቡር ሥራው ሲያቆም ግን ነጋዴዎችም ጠፉ፣ የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሰዎችም ከሥራቸው ተፈናቀሉ፡፡ ሚናስ ትዝብታቸውን ነግረውናል፡- ባቡሩ ሥራውን እንዲያቆም ሲደረግ ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ የምትከፍለው ገንዘብ ከፍ እያለ ሄደ፡፡ አዲሱ የባቡር ጣብያ የቀደመውን ማጠናከር ሲገባው ሀዲዱን ቆርጦት በማለፉ ነው ወደ ጅቡቲና አዲስ አበባ የሚያደርገውን ጉዞ ያቆመው፡፡ ባቡሩ እቃዎችን በቅናሽ ዋጋ ያቀርባል፣ በአንድ ጊዜም በርካታ እቃዎችን ያጓጉዛል፤ ባቡሩ ቢሠራ ኖሮ መንግሥትና ሕዝብ ፈልገው ያጡትን ጥቅም ይሰጣቸው ነበር ነው ያሉን፡፡
የቀድሞው ባቡር ከአዲሱ ባቡር ጋር በቴክኖሎጂ የማይተናነስ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ የምድር ባቡሩን የተቀላቀሉት ዋና ባቡር ነጂ ሙሉጌታ ከበደ ቀደም ባለው ጊዜ ከድሬዳዋ፣ ጅቡቲና አዲስ አበባ ባቡር ነድተዋል፡፡ የድሬዳዋ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከባቡር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ከነበሯት 14 ክፍላተ ሀገራት ወደ ድሬ የማይመጣ አልነበረም በማለት ያንጊዜ ያስታውሳሉ፡፡ “ባቡሩ ለደሀ ከእናት በላይ ሌላ ስም ቢኖር ይሰጠው ነበር፤ እናት ነው፡፡ በድሬዳዋ እንቅልፍ አልነበረም ምግብ የሚያዘጋጀው፣ የሚሸኘው፣ እቃ የሚያቀርበው ሁሉም ሥራ ላይ ነበር ነው” ያሉን፡፡
የአዲስ አበባና የጅቡቲው ጉዞ ከተቋረጠ በኋላ ድሬዳዋ ብዙ ነገር አጥታለች፤ ኢትዮጵያም ብዙ ነገር አጥታለች ነው ያሉት ካፒቴን፡፡ በባቡር ጣብያው ምን አልባትም በቢሊዮን የሚቆጠር እንዳይሠራ የተደረገ ሀብት አለም ብለውናል፡፡ የቀደመው መንገድ በመቆረጡ ሁለት ማሽኖች በጅቡቲ ቆመው መቅረታቸውንም ነግረውናል፡፡ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የጅቡቲ ሕዝቦችም ባቡሩ ሁሉ ነገራቸው ነበርና እንደራሳቸው ያዩት ነበር፣ አብዝተውም ይናፍቁታል፣ ከኢትዮጵያዊያን ጋርም የጠበቀ ወዳጅ አድርጓቸው ነበር ነው ያሉን፡፡ ዋና ባቡር ነጂው እንደነገሩን በቀድሞው የባቡር ጣብያ የትምህርት ማስረጃ ወረቀት የሚያቀርብ ባለሙያ ላይኖር ይችላል፤ ነገር ግን የጠለቀ እውቀት ያለው ባለሙያ አለ፤ የእውቀት ሽግግር እንዲረግ የሚፈልግ ግን የለም፡፡
“የካበተ ልምድና እውቀት ስላለን ባቡር ሲበላሽ እርዳታም አንጠይቅም፤ መንገድ ላይ ጥለንም አንመጣም፤ ጠግነን ይዘን እንገባለን” ብለውናል፡፡ በ1900 ዓ.ም የተሠራው ሐዲድ አሁንም እንደሚሠራ ነግረውናል፡፡ አሳይተውናልም፡፡
የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ድርጅት የድሬዳዋ ምድር ባቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ ተጠሪ ኃይለ ኢየሱስ ደምሰው እንዳሉት ባቡሩ በርካታ ጣብያዎቹን ወደ ከተሜነት በመቀየር ማኅበራዊ ጠቀሜታውን አሳይቷል፤ በወጪና ገቢ የንግድ እንቅሳቃሴ ከፍተኛ አስተዋፆ በማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ ጠቃሜታውን አሳይቷል፡፡ የድርጅቱ ትልቁ ውድቀት የመጣው በዘመነ ኢህአዴግ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የወጭና ገቢው እንቅስቃሴ በመኪና እንዲሆን ተደርጎ ባቡሩ ከእንቅስቃሴ ውጭ እየሆነ ሄደ፡፡ ለባቡሩ ጥገና ይደረግ በሚል ምክንያት ለስድስት ዓመታት አገልግሎት እንዲቆም ተደርጎ እንደነበር ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል፡፡
ከአውሮፓ መንግሥታት በተገኘ በ50 ሚሊዮን ዩሮ ይጠገናል ተብሎ 27 ሚሊዮኑን ተጠቅሞ አንድ ኪሎ ሜትር እንኳን አልተንቀሳቀሰም፡፡ ኮንትራክተሩም ሀገር ጥሎ ነው የጠፋው ብለዋል፡፡ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ነግረውናል፡፡ ድርጅቱም ያለውን አቅም ተጠቅሞ ባቡሩ ከድሬዳዋ-ደወሌ-ግሊሌ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ የባቡር መሥመሩ እንዲሠራ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው ጥያቄዎችን እያቀረቡ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
በጅቡቲ የቆሙት ማሽኖች እንዲሠሩ፣ የተቆራረጠው ሐዲድ በድልድይም ሆነ በሌላ ዘዴ ተስተካክሎ እስከ ወደብ ድረስ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅርበት እየሠሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቱን ለውድቀት የዳረገው ትኩረት መነፈጉ መሆኑን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ መንግሥት ትኩረት እንዲሰጠው ጥረት እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ በመሰል ችግሮች ሩጫው የተገታው ባቡር አሁንም ችግሮቹ ይፈቱለት ዘንድ ይማፀናል፡፡
The post “ሩጫው የተገታው ባቡር” | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.