Quantcast
Channel: Ethiopian News: Trusted, In-Depth Analysis | The Habesha
Viewing all articles
Browse latest Browse all 13069

ካራ ማራን ስናስታውስ፡፡ |የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት

$
0
0

ካራ ማራን ስናስታውስ፡፡

ባሕር ዳር፡ የካቲት 26/2013 ዓ.ም (አብመድ) ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ከውስጥም ከውጭም የማይተኙላት በርካቶች ናቸው፡፡ የዛሬ 42 ዓመታት ወደኋላ በምናብ ብንጓዝ እንኳን በዚህ ወቅት ጦርነት ውስጥ ነበረች፡፡ ሃይልን ፈጣን የመፍትሄ አማራጭ አድርጎ በመጠቀም የሚታሙት የወቅቱ የሀገሪቱ መሪ ኮሎኔል መንስቱ ሃይለማሪያም የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬን ግን በእጅጉ ሳይታገሷቸው እንዳልቀሩ ይነገራል፡፡

የሶሻሊስት ሶማሊያ ርዕሰ ብሄር ጀነራል ዚያድ ባሬ ታላቋን የሶማሊያ ሪፐብሊክ ለመመስረት ድንበራችን እስከ አዋሽ ይዘልቃል ሲሉ በተደጋጋሚ ተደመጡ፡፡ ራዕያቸውን እውን ለማድረግም በድንበር፣ በባህል፣ በእሴት እና በማንነት የሚቀርባቸውን ወንድም የኢትዮጵያ ህዝብ ሊወጉ ጦር አሰልፈው ‹‹ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት›› ብለው ጦርነት አዘመቱ፡፡

ከሐምሌ 1969 ዓ.ም እስከ የካቲት 1970 ዓ.ም ምሥራቃዊዋ የኢትዮጵያ ክፍል ኦጋዴን ለፍልሚያ ታጨች፡፡ እጅግ ሞቃታማ የሆነው የኦጋዴን አካባቢ የኢትዮጵያ ጠረፍ የጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ደግሞ አዋሳኝ ድንበር ነው፡፡ ሶማሊያን ለ21 ዓመታት የመሩት ጀነራል ዚያድ ባሬ ኦጋዴንን በመጠቅለል ታላቋን ሶማሊያ ላንድ የመመሥረት የቆየ ራዕይ እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ ጊዜ አይተው ወቅትን ገምተው ኢትዮጵያ በገንጣይ አስገንጣዮች ትግል የተዳከመች ሲመስላቸው እቅዳቸውን ገቢር ለማድረግ ዳዳቸው፡፡

ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ያሰቡትን ዳር ለማድረስ ያልደገፉት የኢትዮጵያ ጠላት ያልተጠቀሙበት የሴራ መንገድ አልነበረም፡፡ ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ግልፅ ወረራ ከመፈፀሟ በፊት በህቡዕ ተደጋጋሚ ጥቃት በመሰንዘር የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ማዳከም ነበር፡፡ ጦርነቱ በግልፅ በታወጀበት 1969 ዓ.ም ሐምሌ ወር ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት የሶማሊያ ጦር ባልታሰበ መልኩ ወስዶ ጅግጅጋ፣ ሐረርና ድሬድዋ ድረስ ዘልቆ ገባ፡፡

በመጀመሪያ በሶብየት ኅብረት እና በመቀጠልም በአሜሪካ ድጋፍ የነበረው የፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ ጦር ለድል የተቃረበ መሰለ፡፡ የኋላ ኋላ የውጭ ድጋፍ እየቀነሰበት የመጣው የሶማሊያ ጦር የኢትዮጵያ የውስጥ ተገንጣይ ኃይሎች የውስጥ ለውስጥ ድጋፍ ስላልተለየው ጦርነቱን ከመግፋት አልተቆጠበም ነበር፡፡

የፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጦር ወደ ፍፁማዊ ማጥቃት እና እልህ አስጨራሽ ጦርነት መግባቱን የሚያመላክቱ እርምጃዎች መታየት ጀመሩ፡፡ ከኦጋዴን ሞቃታማ ቦታዎች በአንዱ ‹‹ካራማራ›› ከምድርም ከሰማይም እሳት የሚተፉ የጦር አረሮች ምድሪቱን ዘነቡባት፡፡

ታላቋን ሶማሊያ ላንድ የመመሥረት ራዕዩ ጫፍ የደረሰ የሚመስለው ፕሬዝዳንት ዚያድ ባሬ በመጨረሻም ‹‹በዚች ዓለም ላይ ምንም ቋሚ የሆነ ነገር የለም›› ለማለት ተገደደ፤ የዚያድ ባሬ ጦር ድል ተመታ፡፡

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራ እና ተከብራ ትኖር ዘንድ ልምድ አላት እና ራሷን በብቃት ተከላከለች፡፡ ታላቅ ለመሆን የታቀደላት ሶማሊያም በማያባራ ጦርነት ውስጥ ገብታ ፈራረሰች፤ ዜጎቿም ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ያላቋረጠ ስደትን አስተናገዱ፡፡

የካቲት 26 ቀን 1970 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጦር፣ የእናት ሀገር ወዶ ዘማቾች እና 16 ሺህ የሚደርሱ የፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮዋ ኩባ አጋር ወታደሮች ይህን ታሪካዊ ጦር ተቀላቅለው የዚያድ ባሬን ጦር ድባቅ መትተው የኢትዮጵያን አሸናፊነት አወጁ፡፡

የማያልፍ የለም፤ ጠብም ፍቅርም ያልፋል፡፡ ለሚያልፍ ስልጣንና ሐሳብ የሰው ሕይወት ማስከፈል ግን ተገቢ አልነበረም፤ ዚያድ ባሬ ከ41 ዓመታት በፊት ሺዎች እንዲቀጠፉ ምክንያት ነበሩ፡፡ ድርጊታቸው ግን እርሳቸውን ጨምሮ ማንንም አልጠቀመም፡፡

ምንጭ፡- አፍሪካ ፎከስ እና የገብሩ ታሪክ ጥናት

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Source link

The post ካራ ማራን ስናስታውስ፡፡ | የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት first appeared on Satenaw Ethiopian News/Breaking News.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 13069

Trending Articles